በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በወረቀት ላይ የተፈጠረው ሚሊዮን የሥራ ዕድል እና በመሬት ላይ ያለው መራር እውነታ በQR Code እገዳ ምክንያት የታገቱ ስራ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን አጋልጧል።
ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (UAE) በህጋዊ የኮንትራት ሥራ ስምሪት ለመጓዝ ሁሉንም መንግሥታዊና ዓለም አቀፋዊ መስፈርቶች አሟልተው የሥራ ቪዛ (Work Visa) ያገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር (E-LMIS ቢሮ) ያለ በቂ ማብራሪያ የጉዞ መውጫ «QR Code» በመከልከሉ ምክንያት ቪዛቸው እየተቃጠለባቸው እና ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እየተዳረጉ መሆኑን ለ WT Media አስታውቋል።

WT Media ከተጎጂ ዜጎች ያገኛቸውን የሰነድ ማስረጃዎች በመመርመር እንዳረጋገጠው፤ ዜጎቹ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ቀጣሪ ኩባንያዎች (እንደ KRH International Manpower Supply LLC ካሉ ድርጅቶች) ህጋዊ የሥራ ውል (Job Offer Letter) የተቀበሉ ሲሆን ሰነዶቻቸውንም በUAE የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (Ministry of Foreign Affairs) እና በVFS Global በኩል አስፈላጊውን ክፍያ ፈጽመው ህጋዊ ማረጋገጫ (Attestation) ያገኙ ናቸው።
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ተጎጂዎች ለ WT Media እንደገለጹት፤ ለዚህ ህጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ሂደት ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ጊዜያቸውን አጥፍተዋል።

በተለይም ከሁለት ጊዜ በላይ የቃለ-መጠይቅ (Interview) ፈተናዎችን አልፈው፣ የፖሊስ የወንጀል ነፃነት ማረጋገጫ (Police Clearance) ወደ ኦንላይን አሰራር በመቀየሩ ምክንያት ብቻ እስከ አምስት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ በትዕግሥት ጠብቀዋል።
«ለተለያዩ የሰነድ ማረጋገጫዎች፣ ለህክምና ምርመራዎች እና ለኤጀንሲ ሂደቶች ከ70,000 ብር በላይ ወጪ አውጥተናል። አንዳንዶቻችንም ሂደቱ አልቆ ቪዛችን ስለመጣልን በሀገር ውስጥ የነበረንን ሥራ ለቅቀን ለጉዞ ተዘጋጅተን ነበር። አሁን ግን ሁሉንም ህጋዊ መስፈርቶች አሟልተን እያለ E-LMIS ቢሮ የQR Code መከልከሉ ህይወታችንን አመሰቃቅሎታል» ሲሉ አንድ ተጎጂ ምሬታቸውን ገልጸዋል።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በራሱ በኩል ፈተና ተፈትነው ያለፉና ሚኒስቴሩ በመደበላቸው ህጋዊ ኤጀንሲዎች በኩል ፕሮሰሳቸውን የጨረሱ ዜጎች ጭምር በዚህ እገዳ መካተታቸውን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።

ለውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት የሚሰጥ ቪዛ የተወሰነ የጊዜ ገደብ ያለው ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአንዳንድ ዜጎች ቪዛ ጊዜው አልፎበት (Expired ሆኖ) ሙሉ በሙሉ ሲቃጠልባቸው፣ የሌሎች ደግሞ ጊዜው ሊያበቃ የአንድ እና የሁለት ሳምንት ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል።
ተጎጂዎቹ በተወካዮቻቸው በህጋዊ ኤጀንሲዎቻቸው እንዲሁም በUAE በሚገኙ ቀጣሪዎቻቸው አማካኝነት ለሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ «አንዴ ይሰጣቸዋል፣ አንዴ አይሰጣቸውም» ከሚል የተምታታ ምላሽ ውጪ የእገዳውን ትክክለኛ ምክንያት የሚያስረዳ አካል አለመኖሩን ይናገራሉ።
መንግሥት በየወሩ «በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ፈጥሬያለሁ» በሚል ይፋዊ ሪፖርቶችን እያቀረበ ባለበት ወቅት ህጋዊ መንገድን ተከትለው የወጡ ዜጎች በራሱ በመንግሥት መዋቅር እንዲታገዱ መደረጉ በዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ጥያቄንና ቁጣን ቀስቅሷል።
ዜጎች ህጋዊ መንገድን መርጠው ለከፍተኛ ወጪና ኪሳራ መዳረጋቸው ሌሎች ዜጎች ወደ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲገፉ የሚገፋፋ አደገኛ አዝማሚያ መሆኑን ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።
ተጎጂዎቹ ቪዛቸው ሙሉ በሙሉ ሳይቃጠልና የከፋ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ሳይገቡ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጉዳዩን በአስቸኳይ መርምሮ ተገቢውን የ«QR Code» ፈቃድ እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን ይፋዊ ምላሽ እና ማብራሪያ ለማካተት WT Media ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ እስከ አሁን ድረስ ምላሽ ባለማግኘቱ ሊሳካ አልቻለም።