በኢትዮጵያ ከተሜነት ፈጣን እድገት እያሳየ በመሆኑ እንደ ሀገር 5.4 ፐርሰንት የደረሰ ሲሆን በደቡብ ክልልም 7 ፐርሰንት መድረሱም በዎላይታ ሶዶ እየተካሄደ በሚገኘው መድረክ ተገልጿል።
ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረግ ፍልሰት ምክንያት በደቡብ ክልል እየገዘፈ የመጣው ፈጣን ከተሜነት ሊገታ የሚችል ባለመሆኑ ከተሞችን ለኑሮ ምቹ፣ ሰላማዊና ጽዱ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።
ክብርት ኢንጂነር አይሻ እንደተናገሩት ከተሞችን ፅዱ፣ ጤናማና ሳቢ ለማድረግ ጠንካራ የማህበረሰብ ተሳትፎ መገንባትና የአሰራር ደንቦችንና የህግ ማእቀፎችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
“ሀላፊነቱን ተረድቶ በአግባቡ የሚሰራ አመራር ያለበት ከተማ ህይወት አለው” የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ።
አቶ እርስቱ እንደተናገሩት ከተሞችን አረንጓዴ ፣ ጽዱና ለነዋሪው ምቹ ለማድረግ የአመራሩ ትጋትና ተነሳሽነት ወሳኝ በመሆኑ አመራሩ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
እንደ ክልሉ ኮሙኒኬሽን ዘገባ በከተሞች ነዋሪው ተረጋግቶ የሚኖርበት አመራረሩም ተረጋግቶ የሚመራበትና የሚሰራበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት የህግ ማዕቅፍና መመሪያ ወደታች ወርዶ ተግባራዊ መሆን አለበት ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ።


