የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ‘በአገር ግንባታ የምሁራን ሚና’ በሚል ያዘጋጀው አገር አቀፍ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ዑርቃቶ ኢትዮጵያ ከድህነት ጠላቷ ባለፈ የዕጅ አዙር ሃይላት አበይት ጠላቷ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የተዘረጉ የዕጅ አዙር ሃይላትን ለመመከት የምሁራንን የተለየ ጥበብ፣ ዕውቀትና ዕይታ እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።
ምሁራን ቀደም ብሎ በዲጂታል ዲፕሎማሲ፣ በሕዳሴ ግድብና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ለገጠማት አሁናዊ ፈተናም የእነርሱ ልዩ ጥረት እንደሚሻ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ እድገት የተቀረውን አፍሪካ ለመቆጣጠር ስጋት ይሆናል በሚል የውጭ ሃይሎች ስውር እጃቸውን እንደሚያሳርፉ አስታውሰው፤ የዕጅ አዙር ጫናውን የሚመክት የማንቃት ስራ ከምሁራን ይጠበቃል ብለዋል።
ውስጣዊ ችግሮችን ከተሻገርን ውጫዊ ሃይላትን መቋቋም ይቻላል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ምሁራን ለአሁናዊም ሆነ ለቀጣይ ፈተናዎች በተቀናጀ መንገድ በአገር ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አደራ ብለዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በቀሰቀሰው ጦርነት ከፍተኛ ሠብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መከሰቱን አውስተዋል።
በአገር ጉዳይ ችግር ሲከሰት ገለልተኛ መሆን እንደማይቻል ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ካጋጠማት ችግር እንድትወጣ ምሁራን ተጨባጭ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚጠቅባቸው ተናግረዋል።
እንደ ኢዘአ ዘገባ ከሆነ በመድረኩ የመወያያ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ምሁራንም ኢትዮጵያ እያደረገች ባለው የሕልውና ትግል ምሁራን የአርበኝነት መንፈስ መላበስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
