በዳዉሮ ዞን ከ10 ወረዳዎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ማህበራዊ መሰረት ወክለዉ የተገኙ ተሰብሳቢዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ረቂቅ ህገ -መንግስት ላይ ዉይይት እያካሄዱ ይገኛል።
የዉይይቱን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዳዉሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክሌ በዛብህ በእሰሰካሁኑ ሂደት ከዳዉሮ ህዝብ ጋር በቅርበት እየተወያዩ የህዝብን ፍላጎት ማሣካት መቻላቸዉን አስታዉሰዉ በዛሬዉ ቀን ከፕሮጀክት ጽ/ቤት በሚቀርበዉ ረቂቅ ህገ መንግስት ተወያዮቹ ተገቢዉን አስተያየት ይሰጣሉ ብለዉ እንደሚጠብቁ ገልፀዋል።
ረቂቅ ህገመንግስቱን ለተወያዮቹ ያቀረቡት የክልሉ ህገመንግስት አርቃቂ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ብርሃኑ አታሮ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህገ መንግስት ጠንካራ የሆነ የክልል መንግስት ለመመስረት የሚያግዝ ረቂቅ ህገ – መንግስት መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ ብርሃኑ አታሮ አክለዉም ረቂቅ ህገ መንግስቱ የፌደራልና የክልል መንግስት ድርሻ ያገናዘበ የክልሉን ህዝብ ባለቤትነት ስሜት የሚያንፀባርቅና እኩል የመልማትና ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር
የሚያስችል124 አንቀጽ ያለዉ መሆኑን አብራርተዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስተባባሪ ኢንጅነር ምትኩ በድሩ በበኩላቸዉ ክልሉ 13 ነባር ብሄረሰቦች የሚገኙበት መሆኑን አስታዉሰዉ የክልሉ የስራ ቋንቋ ፣የስንደቅ ዓላማ ዓርማ ፣የክልሉ ብሔራዊ መዝሙር ፣የክልሉ ካርታ እና የክልሉ መቀመጫ …ወዘተ በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።