በዎላይታ አከባቢ ከዘጠኝ አመታት በላይ በዘርፈብዙ ልማት ስራዎች ላይ የተሰማራው ሊንክ ኮሙኒቲ ደቨሎፕመንት ኢትዮጵያ የዎላይታ ቅርንጫፍ ለጊዜው መዘጋቱ ተገለፀ

በዎላይታ አከባቢ በተለይም በትምህርት ዘርፍ በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኘው የእንግሊዝ መንግስት በጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው Link community Development Ethiopia ዎላይታ ሶዶ ቅርንጫፍ በአከባቢው በተፈጠረው ከውስጥ እና ከውጭ አለመግባባት የተነሳ ፕሮጀክቱን ለጊዜው መዝጋቱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሰሞኑን የድርጅቱ አመራሮች መታሰራቸውን ተከትሎ ጥፋት እንኳን ቢኖር ድርጅቱ የሚመራበት መመሪያ እና ደምብ ሳይታይ እንዲሁም የቦርድ አመራር ሳያወቅ የተወሰደው እርምጃ የድርጅቱን መልካም ስምና በአከባቢው ድርጅቱ የሰራቸውን በርካታ የልማት ስራዎችን ታሳቢ ያላደረገ ተግባር በመሆኑ ከእንግሊዝ ሀገር የድርጅቱ አመራሮች በመምጣት ስራውን በነፃነት ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እስኪፈጠር የድርጅቱ ፕሮጀክቶች በዎላይታ አከባቢ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ ሙሉበሙሉ ለጊዜው መዘጋቱን የመረጃ ምንጩ በተላይም ለWT ተናግሯል።

ልንክ ኮሙኒቲ ደቨሎፕመንት ኢትዮጵያ በዎላይታ ባለፈው ሰኔ ወር 2012 ዓ ም በአራት ወረዳዎች ላይ በአንድ ቀን አራት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገንብቶ ለማህበረሰቡ ያስረከበ፣ላይብረሪ የሴት ተማሪዎች መመሪያ ማዕከልና ልዩ ዕገዛ በማድረግ እና በየአመቱ ከአንድ መቶ ሚልዮን ብር በላይ መድቦ የተለያዩ ልማቶችን አቅዶ በዎላይታ አከባቢ እየሰራ የሚገኝ አለምአቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅት መሆኑን የድርጅቱ ኃላፊው በፕሮጀክቱ ምረቃ ወቅት ለሚዲያ ከተናገሩት መረጃ ለማግኘት ችለናል።

የአንድ በጎ ድርጅት የራሱን ፕሮጀክት ተገዶ ሳይሆን አከባቢውን ይጠቅማል የሚሏቸውን ስራዎችን የሚያከናውን በመሆኑ ግለሰባዊ ጉዳይን ከድርጅቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያደርስ እርምጃ በመወሰዱ በአከባቢው የድርጅቱ ፕሮጀክት መዘጋቱ ማህብረሰቡን እጅጉን የሚገዳ በመሆኑ ማዘናቸውንም ተናግሯል።

ምናልባት አሁን ላይ የተፈጠረውን ክስተት የሚመለከታቸው አካላት በጥሞና በመመልከት የግለሰቦችን ሳይሆን የማህበረሰብ ዘላቂ ተጠቃሚነትን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነገሮችን ለማስተካከል ፈቃደኝነት ካላቸው ድርጅቱ ለጊዜው የዘጋው ቢሮ በዎላይታ ዳግም የሚቀጥልበት ዕድል ልኖር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተገልጿል።

በተጨማሪም የአካባቢ ተወላጅና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ይሄንን የአከባቢው ማህበረሰብን የሚጠቅም መልካም ዕድል ማጣት ስለሌለበት ድርጅቱ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ በአስቸኳይ መነጋገርና መፍትሔ ማበጀት እንደሚያስፈልግም የመረጃ ምንጩ ለWT አክለው ገልጿል።

Link Community Development Ethiopia በጎ አድራጎት ድርጅት በደቡብ ክልል በዎላይታ አከባቢ ብቻ እንዲሁም በአፋር ፣ ሶሚሊያ፣ ቤንሸንጉልሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች ማህበረሰቡን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ በጎ ስራ እየሰራ የሚገኝ የእንግልዝ አለምአቀፋዊ ድርጅት ነው።

በጉዳዩ ዙሪያ የድርጅቱ አመራሮች ይፋዊ መግለጫ ከሰጡ ዝርዝር መረጃዎችን ተከታትለን እናቀርባለን።