ትናንት የኢፌዲሪ አየር ሃይል በመቀሌ የአሸባሪው ህወሃት ቡድን የወታደራዊ ማሰልጠኛና ማዘዣ ማእከል የሆነውና  የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት ማሰልጠኛ የነበረውን ቦታ በአየር መደብደቡ ይታወቃል።

በዚሁ እለት ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በኩል ፈቃድ የተሰጣቸው ሁለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  የእርዳታ አውሮፕላኖች በመቀሌ እንዲያርፉ በስፍራው ካሉ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ በመከልከላቸው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውም የሚታወቅ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ አውሮፕላኖቹ ከፌደራል መንግስት ፈቃድ የተሰጣቸው እንደሆኑና ወደ አዲስ አበባ የተመለሱትም  በኤርፖርቱ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ በመከልከላቸው ብቻ መሆኑንም አሳውቀዋል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን  የእርዳታ አውሮፕላኖቹ የተመለሱት በየአየር ጥቃቱ ሳቢያ እንደሆነ በማስመሰል የተሳሳተ ዘገባን አውጥተዋል።

የአየር ጥቃቶቹ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተወሰዱና የሽብር ቡድኑ ለእኩይ አላማ የሚጠቀምባቸውን የመገናኛና የወታደራዊ ማሰልጠኛዎችን ብቻ ኢላማ ያደረጉ ናቸው።

የሽብር ቡድኑ ይህንን መሰል የተሳሳቱ መረጃዎችን በማውጣት ህብረተሰቡን በሃሰተኛ ምስሎች ለማወናበድ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ተገንዝቦ ጥንቃቄን መውሰድ እንዳለበት መልእክታችንን እናስተላልፋለን።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

13/02/ 2014 ዓ.ም