
በሱዳን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን መንግስት አስታውቋል።
በሱዳን እየተከናወኑ ያሉ ክስተቶችን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን የገለጸው መንግስት፥ ይህም በሃገራቱ ህዝቦች መካከል ለዘመናት ከኖረው ጠንካራ የወንድማማችነት ትስስር የመነጨ መሆኑን አንስቷል።
መግለጫው የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን ከሲቪል እና ወታደራዊ አካላት የተውጣጣ ጥምር መንግስት እንዲመሰረት እና የሽግግር ጊዜ ህገ መንግስት ሰነድ እንዲዘጋጅ ጉልህ ሚና መጫወቱን አስታውሷል።
አሁን ላይም በሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠርና ሁሉም ወገኖች ወደ ሰላም የሚወስዳቸውን ማንኛውንም ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪውን አቅርቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳን ወደ ዴሞክራሲ ያደረገችውን ሽግግር እንደሚደግፍና የሽግግር ዘመኑን ሕገ መንግሥታዊ ሰነድ ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍም ነው የገለጸው።
ኢትዮጵያ የሱዳን ሉዓላዊነት መከበር እንዳለበት እና የውጭ ጣልቃ ገቦች በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸውም ገልጻለች።
የሱዳን ህዝብ እነዚህን ተግዳሮቶች ለማለፍና የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚችል እምነቱ መሆኑንም መንግስት በመግለጫው አመላክቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ እንደ ሁልጊዜው ከሱዳን ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፍላጎት ጋር ጸንቶ እንደሚቀጥልም ነው በመግለጫው አብራርተዋል።