
በያዝነው የምርት ዘመን ከ70 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ገለፁ።
በደቡብ ክልል በያዝነው የምርት ዘመን ከ70 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ገለፁ።
የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት በክልሉ ያለውን ሰፊ የመሬት ሀብትና ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና በምግብ ራስን ለመቻል የተቀናጀ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።
የክልሉን መንግስት በመወከል መግለጫ የሰጡት የቢሮ ሃላፊዋ በክልሉ የኤክስፖርት ምርትን ስፋትና ጥራት ለማሳደግ የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል ።
በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት የክልሉን ሰፊ የመስኖ እድልና አማራጭ በአግባቡ ተግባር ላይ በማዋል የመስኖ ስንዴ ልማትን በማስፋፋት ግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ በተቀናጀ ሁኔታ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።
ለዚህ ልማትም 170 የሚሆኑ አነስተኛ መስኖ ተቋማት ወደ ስራ እንደሚገቡ አስረድተዋል ።15 ሺ ሄክታር መሬት ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ ስንዴ ልማት እንደሚሸፈንም ገልጸዋል ።
በአጠቃላይ በያዝነው የምርት ዘመን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በልዩ ልዩ ሰብሎችና አዝርእቶች በማልማት 71 ሚሊዮን ኩንታል አጠቃላይ ምርት ለመሰብሰብ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ ሰናይት እስከ አሁን ባለው ሂደት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል ። ከዚህ ውስጥ 155ሺ ሄክታር መሬት በመስኖ የሚለማ ይሆናል።
ከዚህ ስኬት መንግስት በየደረጃው ያለውን ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እንዲሁም የግብኣት አቅርቦት ለማጎልበት እንደሚሰራም ጠቁመዋል ።
በዚህ ወቅት በክልሉ የቡና፣የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ጥራት ያለው የአቦካዶ ምርትን በተገቢው መንገድ ለማሳደግ እየተሰራ ነው ሲሉም ሃላፊዋ አክለዋል።