
“በርካታ አመታትን የተሻገረው ታማኝነት ባለቤት” የአቶ ታደሰ መርዕድ ከዎላይታ ዳሞት ፑላሳ እስከ ሀገር ባለውለታነት
“አጥሩን ቆርጠው አሻገሩኝ”
የዛሬው የፌደራል ጉሙሩክ ኮሚሽን የሐዋሣ ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ መርዕድ፣ የተወለዱት በቀድሞ ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ወላይታ አውራጃ ዳሞት ጋሌ በሚባል ወረዳ ዛሚኔ ውሊሾ ቀበሌ ነበር፡፡ ቀኑ ደግሞ ህዳር 15/1961 ዓ.ም። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል በሻንቶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ፡፡ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በቦዲቲ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡
11ኛና 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ደግሞ በአረካ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀዋል፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከተፈተኑ በኋላ በጊዜው በ1981 ዓ.ም አርባ ምንጭ መምህራን ማሠልጠኛ ተቋምን በመቀላቀል የአንድ ዓመት ሥልጠና መውሰድ ቻሉ፡፡
በዚያው ዓመት መጨረሻ በኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ፓታታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተቀጥረው ማገልገል ጀመሩ፡፡ ሐምሌ ወር 1981 ዓ.ም ደግሞ ሥራቸውን የጀመሩበት ጊዜ ነበር፡፡ በት/ቤቱ ሁለት ዓመት ከግማሽ ካገለገሉ በኋላ ወደ ዳሞት ጋሌ ወረዳ ሱቄ ባቃላ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛወሩ፡፡ በዚያም እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡ በመቀጠል ወደተወለዱበት ቀበሌ ዛሚኔ ውሊሾ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማምራት ለአንድ ዓመት አገልግለዋል፡፡
ከዚያም የመምህርነት ሥራን በመልቀቅ ወደ ሌላ ሥራ ተሸጋግረዋል፡፡ “በሥራ ላይ ያጋጠሙ ነገሮችን በሙሉ ማስታወስ ከባድ ነው” ይላሉ፡፡ ነገር ግን መምህር ሆነው ሲሠሩ በርካታ ነገሮች እንደገጠማቸው ይገልጻሉ፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ የተመደቡበት ቦታ ከወረዳው ርዕሰ መዲና በእግር የስድስት ሰዓት መንገድ ይጓዙ ነበር፡፡ አካባቢው ተሽከርካሪም የሚገባበር አልነበረም፡፡ የሚያስተምሩበት ቦታ ከተወለዱበት ቦታ አቀማመጡ በጣም ይለያል፡፡
ትምህርት ቤቱ የሚገኘው በጣም ተራራማ፣ ቁልቁለታማና ውጣ ውረድ በበዛበት ቦታ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ በየወሩ ያንን ተጉዘው ከተማ በመምጣት ደመወዝ ስለሚወስዱ በሥራውና በግል ህይወታቸው አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድር ነበር። ያኔ ምንም እንኳ ወጣት የነበሩ ቢሆንም ፈታኝ ሁኔታ ማሳለፋቸውን ይናገራሉ፡፡ እዚያ ትምህርት ቤት ሲመደቡ የገረማቸው ነገር በዚያ አካባቢ አንድም ሴት በወቅቱ ትምህርት እንድትማር አለመፈቀዱ ነበር፡፡
በኋላ “ለምንድን ነው ሴት ልጅ ትምህርት የማትማረው? ለምን ትምህርት ቤት አታስገቡም?” ብለው ቤት ለቤት ዞረው አርሶ አደሮችን መጠየቃቸውን ያስታውሳሉ። ሆኖም “ሴት ጓዳ ነው እንጂ መሆን ያለባት፡፡ እንዴት ወደ ውጭ ትወጣለች” የሚል ምላሽ ነበር ያገኙት፡፡ ከዚያ ከወጡ ከ20 ዓመት በኋላ ተመልሰው ሲሄዱ ግን እስከ 8ኛ ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ወንዶችና ሴቶች በእኩል ቁጥር ሲማሩ ማየታቸውን ይናገራሉ።
ከመምህርነት እንደለቀቁ በታህሳስ 1/ 1988 ዓ.ም በዳሞት ጋሌ ወረዳ ምክር ቤት በተካሄደው ምርጫ የሥራ አስፈጻሚ አባል ሆነዋል፡፡ እንዲሁም የወረዳው ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ሃላፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ ሆነው መሾማቸውን ይናገራሉ። ከ1990 ሚያዝያ ጀምሮ እስከ መስከረም 1993 ድረስ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ማገልገል ችለዋል፡፡
አቶ ታደሰ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ከጓደኞቻቸው፣ ከማህበረሰቡ፣ ከአለቆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው በርካታ ልምድ በመቅሰማቸው ራሳቸውን ማሻሻላቸውን ያስረዳሉ፡፡ ትምህርት ቤት ገብተው ከተማሩት ሙያ በተጨማሪ በሥራ ህይወታቸው ብዙ ዕውቀት ማግኘታቸውንም ይናገራሉ።
ይህ ደግሞ ብዙ ተግዳሮቶችን በትዕግሥት እንዲያልፉ አድርጓቸዋል፡፡ በዎላይታ ዞን በዳሞት ጋሌ ወረዳ በኃላፊነት በሚሠሩበት ወቅት ህብረተሰቡ በቋንቋችን እንናገር ብሎ ጥያቄ በሚያቀርብበት ጊዜ የወቅቱ ሥርዓት አራማጆች ጫና ማሳደር ፈልገው ነበር፡፡ ይህንን ጫና በመቋቋም ህዝቡ በአንዳንድ ቦታ ጉዳት የደረሰበት ቢሆንም በራሳቸው በኩል ህዝቡን እንዳይጎዳ መርዳታቸውንና በሳል አመራር መስጠት መቻላቸውን ይገልጻሉ፡፡
የታጠቀ ኃይል ጉዳት እንዳያደርስና ህዝብም ተገቢውን ጥያቄ በሰከነ ሁኔታ እንዲያቀርብ በማድረግ ከወጣቱም ጋር ተግባብቶ ለመስራት የስራ ልምዴ ልምድ ብዙ ረድቶኛል ይላሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ለብቻቸው እንዳልሆኑ በጋራ ሠርተው ለውጤት መብቃታቸውን ይናገራሉ፡፡ አቶ ታደሰ የወረዳ ሃላፊ ሆነው በኃላፊነት በሚሰሩበት ወቅት በህብረተሰቡ ዘንድ ተወዳጅ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡
ለዚህም በማሳያነት አንድ ገጠመኛቸውን እንዲህ ሲሉ ያስታውሳሉ፡- “በአንድ ወቅት መንገድ ጠፍቶብኝ በአንድ ሰው እርሻ ላይ አቋርጬ ለማለፍ ስሞክር ባለይዞታው ከእሩቅ አይቶኝ ‘እርሻዬን በመሀል ሰንጥቆ የሚመጣው ይህ ደፋር ማነው?’ ብለው መጥረቢያ ይዘው ይጠብቁኝ ነበር። ልክ ስደርስ መውጫ በሩ በአጥር ተዘግቶ ነበር፡፡ በጣም የተቆጡት አርሶ አደሩ እኔን አይተው ‘አንተ ነህ እንዴ? አንተማ እንኳን በመሬቴ እኔ ተኝቼ በእኔ ላይ ብትሄድም ደስ ይለኛል’ አሉ፡፡ አጥሩንም ቆርጠው አንስተው አሻገሩኝ፡፡
በጊዜው ምን ውለታ እንደሠራሁ አልጠየቅኩም፡፡ ነገር ግን በኋላ በፈጸምኩት መልካም ተግባር ስለመሆኑ ሰማሁ፡፡ መልካም አገልግሎት መስጠት በተገልጋይ ዘንድ ተወዳጅ ያደርጋል” ከ1994 እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ተምረዋል፡፡
በዚህም በሒሳብ አያያዝ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል። ከዩኒቨርሲቲው ከተመረቁ በኋላ ከ1997 እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ የዎላይታ ሶዶ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡
ያልተነገረለት ጀግና
በሶዶ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ ከተማው እንዳሁኑ ውበት የተላበሰ እንዳልነበር ይጠቁማሉ፡፡ ክረምት ላይ ከፍተኛ ጭቃና ጎርፍ ስለነበረ ሰው መንቀሳቀስ የማይችልበት ነበር፡፡ የዎላይታ ዩኒቨርስቲ እንዲገነባ የተፈቀደው በ1997 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ የዩኒቨርስቲው ግንባታ ከተፈቀደ በኋላ መነቃቃቱ የመጣ ቢሆንም በዋናነት የሶዶ ከተማ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድርና በጀርመን ተራድኦ ድርጅት ድጋፍ በጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ማሳመር ተችሏል፡፡ ለዚሁ ሥራ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡
ከ2001 እስከ ህዳር 2004 ዓ.ም ድረስ የወላይታ ዞን ገቢዎች ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በዚህ ወቅት በዘርፉ የሚታየውን የሥነ ምግባር ችግር መቅረፍ ችለው እንደ ነበር አቶ ታደሰ ያነሳሉ፡፡ በተለይ የአካባቢው ማህበረሰብ የመንግሥትን ግብር በአግባቡ እንዲከፍል ማስተማራቸውንም ያስታውሳሉ፡፡ ሠራተኛውም ሥራውን በአግባቡ እንዲሠራ ወረዳዎችንና ከተማ አስተዳደሮችን በማስተባበር ግብር በአግባቡ እንዲከፍሉና ደረሰኞችን እንዲቀበሉ በማድረግ የመንግሥት ገቢ እንዲጨምር የራሳቸውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡
እነዚህን ሥራዎች ሲሠሩ አብዛኛው ሰው የተቀበለ ቢሆንም በአንጻሩ ደግሞ ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ የተወሰኑ ግለሰቦች በህገ ወጥና በኮንትሮባንድ ንግድ ለመሰማራት በመፈለጋቸው ምክንያት በህጋዊ መንገድ መሥራት አልቻሉም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳዎችና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር በመቀናጀት ህገ ወጥነትን ለመከላከል ጠንክረው ሠርተዋል፡፡
ያኔ የተጀመረ በጎ ጅምር በመኖሩ የሶዶ ከተማ ዓመታዊ ገቢ ወደ 4 ሚሊዮን ከፍ ብሎ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በየጊዜው እየጨመረ የሄደው ገቢ ከመጀመሪያው ጥሩ መሠረት በማስያዛቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከታህሳስ 1/ 2004 እስከ ታህሳስ 2006 ዓ.ም ድረስ የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡
በዚህ ወቅት አጠቃላይ ዞኖችን፣ ልዩ ወረዳዎችንና ወረዳዎችን በማገዝ ገቢዎችን የሚመለከቱ መመሪያዎች፣ ደንቦችና አሠራሮችን በማዘጋጀት በቴክኖሎጂ የተደገፉ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ክልል ላይ ተንጠልጥለው የቆዩ በርካታ ጉዳዮች በየከተማ አስተዳደሩና በየዞኑ ወደ ክልሉ መዲና እንዳይመጡና እዚያው አገልግሎት እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡
ችግር የሚፈጥሩትን በማረም ተጨማሪ እሴት ታክስ ለመክፈል ወደ ሀዋሳ የሚመጡ ግብር ከፋዮች አገልግሎቱን በቅርበት እንዲያገኙ አድርገዋልም፡፡ የአቶ ታደሰ መርዕድ ኃላፊነት በዚህ አላበቃም፡፡ ከታህሳስ 2006 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት የፌዴራል ተወካዮች ምክር ቤት አስፈጻሚዎችን እንደገና ለማደራጀት ባወጣው አዲስ አዋጅ መሠረት ገቢዎች ሚኒስቴር ሆኖ ተቋቋመ፡፡ የጉሙሩክ ኮሚሽን ደግሞ ተጠሪነቱ ለገቢዎች ሚኒስቴር ሆኖ ራሱን ችሎ በኮሚሽን ደረጃ ተዋቀረ፡፡
በዚህ መሠረት ከ2001 አጋማሽ ጀምሮ በኢፈዴሪ የጉሙሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን እስካሁን ድረስ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በስራው ዓለም ካካበቱት ልምድ በመነሳት “ሥራን በጋራ በመግባባት መሥራት ያስፈልጋል” ሲሉ ይመክራሉ፡፡
በተለይም የሀገሪቱ ተስፋ የሆኑት ወጣቶች በጋራ ቢሠሩ ማደግ እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ በጥቅሉ ግን በመንግሥት ሥራም ሆነ በንግድ የተሰማሩ በሙሉ በቅንነትና በታማኝነት ህብረተሰቡን ቢያገለግሉ ሀገሪቱን ማሻገር እንደሚችሉ እምነታቸው መሆኑን ደሬቴድ ዘግቧል፡፡
