የኢትዮጵያ ሕዝብ በረዥም የጊዜ ሂደት በእርስ በርስ ጋብቻና በሌላም መንገድ የተዋሄደ ነው፡፡ በተለይም ከሚንገምተው በላይ በእርስ በርስ ጋብቻ የተዋኸደ (highly intermarried) በመሆኑ ማንንም ከማንም መለየት በማይቻል ደረጃ ተመሳሳይ ባሕርያትን (common traits) የሚጋራ ነው፡፡ እንዲያው በቲኦሪ ደረጃ ጥንት እንዲህ ነበር ለማለት ካልሆነ በስተቀር አንድን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሌላው በቀለም ፍረጃ ለያይቶ መመደብ የማይቻል ነው፡፡ በዘሬ አውድ ማን ኩሽ ማን ሴም እንደሆነ መለየት አይቻልም፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ አንድ ሆኖ የተሰናሰለውን ሕዝብ ነጣጥሎ አንዱን ሴም ሌላውን ደግሞ ኩሽ አድርጎ በቀለም ፍረጃ የመምራት ፍልስፍና (Racial ideology) ከ1980 ወዲህ ወይም በዘመነ ኢህአዴግ የተመራንበት ሳይሆን የዚህችን አገር ሕዝብ ለበርካታ ምዕት ዓመታት የከፋፈለ ነው።
የሰው ልጅ በችሎታውና በተራማጅ አስተሳሰቡ በሚመዘንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሴማዊ ሆንክ ኩሻዊ ችሎታ እስካለህና አስተሳሰብህ ተራማጅ እስከሆነ ድረስ ከተቀያያሪ ዓለማዊ ሁኔታ ጋር መጓዝ ትችላለህ፡፡ ከሴም ነገድ ተመደብክ ከኩሽ ሰው ነህ፡፡ አንዱን አጀግነህ ሌላውን አሳንሰህ ታሪክ በመጻፍህ የጻፍክለትን ማኅበረሰብ ከሰውነት ወደ መልአክነት አትቀይረውም። ሰው ሰው ነው። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሟች ነው፡፡ የማናችንም አባት አዳም ነው፡፡ ትንሽ ወዲህ ጠጋ አድርገን ከቆጠርን ደግሞ የሁላችንም አባት ኖህ ነው። ጥረው ግረው በላባቸው በወዛቸው ሳይሆን ሳይሠሩ የመብላት አባዜ የተጠናወተባቸው በአምሳለ አምላክ የተፈጠረውን የሰው ልጅ ከሚዛናዊ የእኩልነት መለኪያ አውርደው በአናሳ አብልጫ ትርክት እየመዘኑ እርስ በርስ የማይደማመጥ እስኪሆን ድረስ ከፋፍለዋል።
የቀለም ፍረጃ ፍለስፍና አቀንቃኞችና አሽከሮቻቸው የዘሩትና የተከሉት የክፉ አረም ፍሬ ተጠብቆ በቀጣይ ትውልድ አዕምሮ እንዳይበቅልና እንዳይፀድቅ ለማድረግ ለሐቅ የቆሙ ምሁራን በታሪካዊ እውነታ ላይ የተመሠረተ ሙግት በማድረግ ቀጣይ ትውልድ በመከፋፈል ሳይሆን በአንድነት፣ በመገፋፋት ሳይሆን በመደጋገፍ፣ ጠልፎ በመጣል ሳይሆን በመተጋገዝ ወደፊት የሚጓዝ እንዲሆን የማስቻል ታሪካዊ ኃላፊነት ልንወጣ ይገባል ።
በዳንኤል አንጋሞ

