ሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተጠራው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ቦምብ በመወርወር የሰው ህይወት ያጠፉ አምስት ግለሰቦች በተመሰረተባቸው የሽብር ወንጀል ክስ ከ5 ዓመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ።
ጌጡ ግርማ፣ ብርሃኑ ጃፋር፣ ጥላሁን ጌታቸው፣ ባህሩ ቶላ እና ደሳለኝ ተስፋዬ ናቸው ተከሳሾቹ።
ሁሉም ተከሳሾች ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ ከግምት ውስጥ ያስገባው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት በተከሳሾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔውን አሳልፏል።
በዚሀም መሰረት ጌቱ ግርማ በ23 ዓመት፣ ብርሃኑ ጃፋር በ22 ዓመት እና ባህሩ ቶላ በ17 ዓመት ፅኑ እስራት ሲቀጡ፣ ቦምብን አፈንድቶ ለሁለት ሰዎች ህይወት ማለፍ እና ለበርካቶች መቁሰል ምክንያት የሆነው ጥላሁን ጌታቸው በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተቀጥቷል።
ወንጀሉን ማሳወቅ ሲገባው የሸሸገው ተስፋዬ ደሳለኝ ደግሞ በ5 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጥቷል።
በወቅቱ ብርሃኑ ጃፋር ለዚህ የሽብር ድርጊት የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥበት የነበረው ተሽከርካሪ በመንግስት ውርስ እንዲሆን ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል ሲል ኢብኮ ዘግቧል።

