የዎላይታ ህዝብ የአሜርካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለግብጽ በመወገን ኃላፊነት በጎደለው አኳኋን ያሰተላለፉትን መልዕክትን አወግዘዋል፡፡

ታላቁ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ህዝብ እውቀት፣ ጉልበት እና ሃብት በሉዓላዊ ምድር የሚገነባ አንጡራ ሀብት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ህብረተሰብ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ እሰከአሁን ከሁለት መቶ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የዞኑ ህዳሴ ግድብ ማሰተባበሪያ ምክር ቤት አስታውቋል።

የዎላይታ ህዘብ እስካሁን ከ206 ሚሊዮን ብር በላይ ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ አድርገዋል

የዎላይታ ዞን ነዋሪ የሆኑት አቶ ታምራት ስልጤ እና አቶ አማኑኤል መና በሰጡት አሰተያየት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድህነትን ድል የሚናደርግበት በመሆኑ ለድርድር የማይቀርብ የሉዓላዊነታችን መገለጫ ነው፤ግድቡ እንደዓይን ብለናችን የሚንሳሳለትና በእኛው ጉልበት፣ እውቀትና ገንዘብ የሚገነባ ሀገራዊ ልማት እውን የሚናደርግበት ፕሮጀክት ነው ሲሉ አሰተያየት ሰጪዎች አስረድተዋል፡:

እንደ አስተያየት ሰጪዎች ገለጻ ፕረዝዳንት ትራምፕ በህዳሴ ግድባችን ዙርያ የሰጡት መግለጫ እውነታውን ያላገናዘበና መሰረተ ቢስ በመሆኑ ህዝቡ እንደወትሮው ሁሉ ለግድቡ ስኬታማነት በአንድነት እንዲነሳሳ የሚያነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለአራት ዙር ከደመወዛቸው ቦንድ የገዙት ወ/ሮ ፅጌ ወርቅነህ ግድቡ ከዳር እንዳይደርስ ከአሜርካው ፕረዝዳንት በኩል የተሰነዘረው የማስፈራሪያ ቃላት እጅግ አሳዛኝና ከአንድ ሀገር መሪ የማይጠበቅ መግለጫ መሆኑን ተናግረዋል፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ የሀገራችን ሴቶች ከችግርና ከድካም ተላቅቀው ወደ ዘመናዊ ኑሮ ለመሻገር ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት መሆኑን አሰተያየት ሰጪዋ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሰጡት አስተያየት ሉዓላዊነታችንን የሚጋፋ መግለጫ መሆኑንና ይህ ድርጊት ኢትዮጵያውያንን አንድነታቸውን አጠናክሮ ግድቡን ከዳር ለማድርስ የሚያነሳሳ ቁጭትና እልህ የፈጠረ ነው ሲሉ የወላይታ ዞን የህዳሴ ግድብ የህዝብ ተሳትፎ ማሰተባበሪያ ምክር ቤት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘርገኔ ወይሻ አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ እስከ መስከረም 30/2013 ዓ.ም ድረስ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለግድቡ ግንባታ ከ206 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ ገቢ መደረጉን ከዎላይታ ዞን የህዳሴ ግድብ የህዝብ ተሳትፎ ማሰተባበሪያ ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ሲል የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዘግቧል።