በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ የአሸባሪው የሕወሓት ጁንታ በሀገር ላይ እያደረሰ ያለውን ሀገር የማፍረስ አደጋ ለመቃወምና የውጭ ሀገር ሚዲያ የውሸት ዘመቻ ለማውገዝ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ንግግር ያደረጉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ክብር ተጠብቆ እንዲቆይ መላው የዳውሮ ህዝብ ለአፍታም ቢሆን እንደማይዘነጋም ተናግረዋል።
ለሀገራችን ነፃነትና ሉአላዊነት የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ያሉት የታርጫ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ ጎደቶ በበኩላቸው መከላከያ ሰራዊትን መደገፍ፣ ግንባር መዝመትና አከባቢን መጠበቅ ከሁሉም ኢትዮጵያን የሚጠበቅ ሀላፊነት ነው ብለዋል።
ከንቲባው አያይዘውም የኢትዮጵያ አንገት መድፋት የመላው አፍሪካና የአለም አንገት መድፋት ስለሆነ ኢትዮጵያ ቀና እንዲትል ሁሉም የከተማውና የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ቆሞ የኢትዮጵያን አንገት ለማስደፋት የሚንቀሳቀሱትን በጋራ መመከት እንደሚገባ ተናግረዋል።
እንደ ዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘገባ በተባበረ ክንድ የጁንታውን ቀብር እናፋጥናለን ያሉት ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክለ በዛብህ መላው የዳውሮ ህዝብ እንደ ከዚህ ቀደሙ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚደርገውን ሁሉ አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ ለየትኛውም ወራሪ ሀይል ተሸንፋ የማታውቅ የነፃነት ሀገር ናት ያሉት የሰልፉ ታዳሚዎች ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስጠብቃ እንዲትቀጥል የትኛውንም ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ ገልፀዋል።
