ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ጊዜያት ትኩረት ተሰጥቷቸው በሚሰሩ ሥራዎች ዙሪያ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በዛሬው ዕለት የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር፣ ከዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ፣ የየዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ በየዘርፉ ከሚገኙ ዳይሬክቶሬቶች እንዲሁም ከመምህራንና አስተዳደር ሠራተኞች ጋር ውይይት መደረጉንና ቀጣይ ትኩረት ተስጥቷቸው  በሚሰሩ ሥራዎች ዙሪያ ውይይት መካሄዱን ፕሬዝዳንቱ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁመዋል፡፡

ቀጣይ ትኩረት ተስጥቷቸው ከሚሰሩ ተግባራት መካከል ዋንኛው አበይት ተቋማዊ ችግሮችን ለይቶ በመፍታት መልካም አስተዳደርን ማስፈን እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ገልፀው፤ እንደ ተቋም የተጀመሩትን ፈጣን የለውጥና የልማት ጉዞን በትምህርትና በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝብ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ሥራ በተያዘው በጀት ዓመት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ በመሰረተ ልማትና ግንባታ የሥራ መስክ  የጥራትና ወቅታዊነት ችግሮችን በመፍታት እንደተቋም የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ተወዳዳሪ፣ አረንጓዴ፣ ጽዱ፣ ሰላማዊና ህብረ ብሔራዊ ተቋም የመገንባቱ ሥራ የበለጠ ዳብሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት እንደተቋም የተጀመሩ የትምህርትና የምርምር ጥናትና አግባብነት ተግባራት አወንታዊ ውጤት ቢያስመዝግቡም፤ በቀጣይ ጊዜያትም የትምህርት፣ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ጥራታቸው ተጠብቆ በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆኑ የድጋፍና ክትትል ተግባር ይቀጥላል ሲሉ ፕሬዝዳንቱ አሳውቀዋል፡፡ 

ብልሹ አሰራርን የማከሰም ሥራ የቅድሚያ ቅድሚ እና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፤ ለመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራር መንስዔ የሆኑ ተግዳሮቶችን በመለየት እና በመከላከል ሁለንተናዊ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት በመቀናጀት እንደሚሰራም ተናግረዋል በመግለጫቸው፡፡ 

ወቅታዊ፣ ጥራትና ታዓማንነት ያለው ተቋማዊ መረጃን አግባብነት ባላቸው ህጋዊነት ባላቸው ተቋማዊ የህትመት፣ የማህበራዊ ትስስር እና ኤሌክትሮኒክስ ሚድያዎችን በመጠቀም መረጃ የማሰራጨት ሥራ ተቋማዊ የአደረጃጀት ሥርዓትና የመረጃ ፍሰት ሥርዓት ጠብቆ እንዲሄድ በተቀናጀ መልኩ እንደሚሰራም ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል፡፡ 

እንደ ተቋም የተጀመሩ የልማትና የለውጥ ሥራዎች በጠንካራ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላት የተቋሙን ራዕይ በመጋራት የዩኒቨርሲቲውን ትልም እንዲያስቀጥል ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ጥሪ አቅርበው፤ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ሥርዓት በመዘርጋት ወቅታዊ ግብረ መልስ ለመስጠት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ዝግጁ መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡