በሥልጠና መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መስፍን ቢቢሶ፤ ዩኒቨርሲቲው በ1999 ዓ.ም ከተቋቋመ ወዲህ በርካታ የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ መቆየቱን ገልፀዋል።

የዎላይታ ዘመን መለወጫ በዓል”ጊፋታ” በዩኒስኮ ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት ታሪክ አዋቂዎች ገንቢ አስተያየት በመስጠት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረከቱ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ዩኒቨርሲቲው የጊፋታ በዓል በዩኒስኮ ለማስመዝገብ አስፈለጊውን ትብብር እያደረገ መቆየታን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠቁመው፤ የጊፋታ በዓልን በዩኔስኮ ማስመዘገብ ብቻ ሳይሆን ከተመዘገበ በኋላም ለአካባቢው ማህበረሰብ ምን ጥቅም ይሰጣል የሚለው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።

አቶ ተሾመ ሀብቴ በወላይታ ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው ባህል የሌለው ህዝብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማይታወቅ መሆኑን ገልፀው፤ ባህሉም ሆነ ህዝቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ እንዲሆን የዎላይታ ዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” በዩኒስኮ/UNESCO እንዲመዘገብ ከዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር በስፋት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የጊፋታ በዓል በዩኔስኮ ሲመዘገብ የዎላይታ ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፤ የባህል ዕውቀት ላይብራሪ የሆኑት የሀገር ሽማግሌዎች ያለቸውን የባህል ዕውቀት ለትውልድ እንዲያስረዱ አሳስበዋል፡፡

አቶ ተሸመ አክለውም የጊፋታ በዓል ትውልድ ተሸጋሪ እንዲሆን እያንዳንዱ አካል ለባሕላዊ እሴቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ባህሉን ማክበር እንዳለበትና በዓሉን በማልማት የድርሻው ሚና መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

አቶ አበበ ኃይሉ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ከፍተኛ ተመራማሪ ሲሆኑ የዩኒስኮ/ UNESCO ኮንቨንሽንን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የያዘ ሰነድ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡

የዎላይታ ዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” በዩኒስኮ/UNESCO እንዲመዘገብ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለጹት ከፍተኛ ባለሙያው፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ከሃያ በላይ ሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት አባል በመሆኗ ይህን ሥራ የዕቅድ አካል በማድረግ እየሰራች እንደሆነም ጠቁመዋል።

በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አበሻ ሽርኮ በበኩላቸው የወላይታ ዘመን መለወጫ “ጊፋታ” በዓል በዩኒስኮ/UNESCO እንዲመዘገብ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን፣ የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና የዎላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በጋራ የመግባቢያ ሰነድ በመፈረም ወደ ሥራ የገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ናሽናል ኢንቨንተሪ በማዘጋጀት ለዩኔስኮ የመላክ፣ እስከ10 ደቂቃ የሚፈጅ ዘጋባ (ዶክመንታሪ) ፊልም በማሰራት የመላክ እና ሕጋዊ አካሄዱን የመከታተል ሥራ እየተወጣ እንደሆነም ዶ/ር አበሻ ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር አበሻ አክለውም፤ የዎላይታ ብሔር ካላንደር መሥራት፣ የዎላይታ የታሪክ አፃፃፍ (Historiography) የተመለከቱ ጉዳዮችን የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እየሰራ እንደሆነ እንዲሁም ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ሚድያዎች ባህሉን የማስተዋወቅ እንዲሁም ስለባህሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች የመስጠት ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የዎላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የአስተዳደር ጉዳዮች ማለትም ከህብረተሰብ የስምምነት ፊርማና የጥናቱን መረጃ የማሰባሰብ እንዲሁም የምዝገባ አካሄዱን የመከታተል ሥራን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑንም አውስተዋል።

በስልጠና መድረክ የጊፋታ በዓል በዩኔስኮ ሲመዘገብ ለማህበረሰብ ያለው ፈይዳ የሚመለከት ሰነድ በአቶ አበራ አንጁሎ የቀረበ ሲሆን፤በዎላይታ ብሔር ውስጥ የተለያየ ተፅዕኖ ጊፋታን እንዳላጠፋው፣ የዎላይታ ብሄር ጊፋታን እንደዘመን መቁጠሪያ እንደሚጠቀም በቀረበው ሰነድ ተገልጿል።

የተለያዩ የዎላይታ ብሄር ክዋኔዎች፣ ሁኔቶች፣ ልማዶች፣ ወጎች፣ የሊቃ ሥነ_ሥርዓት ወዘተ በጊፋታ እንደሚከናወኑና እና በዓሉ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ ጥንታዊ የብሄሩ እሴት መሆኑን በስልጠናው ተሳታፊዎች ተጠቁሟል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች እና ሌሎች ታዳሚዎች የጊፋታ በዓል በዩኔስኮ እስኪመዘገብ ድረስ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል በመግባት የስምምነት ፊርማቸውን ማስቀመጣቸውን ከዩንቨርስቲው ኮሙኒኬሽን ዳይረክቶሬት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: