የዎላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል በ50 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ግንባታ መጀመሩ ተገለፀ ፡፡

ግንባታው ሆስፒታሉ ለአከባቢው ማህበረሰብ የሚሰጠውን ህክምና አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተሻለ ጥራት ለመስጠት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

የዎላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል በ1997 ዓ.ም ተቋቋሞ ለበርካታ ዜጎች የህክምና አገልግሎት በመስጠት የሚታወቅ ተመራጭ የህክምና ተቋም በመሆን እያገለገለ ይገኛል።

ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት የተገልጋዮችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን በጥራት እና በስፋት ለመስጠት በ50 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ግንባታ ጀምሯል።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ከበደ የግንባታው መጀመር ከዚህ በፊት በሆስፒታሉ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን በጥራትና በስፋት ከመስጠት በተጨማሪ አገልግሎት ለማግኘት ከሩቅ ቦታ መጥተው ተራ በመጠበቅ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ለሚያባክኑ ወገኖች እፎይታ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ተጨማሪ ግንባታ ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ ደረጃ ከዚህ በፊት ያልተጀመረ የህክምና አገልግሎት በዘመናዊ መሳሪያዎች እንደሚጀመርም አቶ ኤፍሬም አክለው ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት የተጀመረው ተጨማሪ የሆስፒታሉ ግንባታ በአንድ አመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን ለአከባቢው ማህበረሰብ ተጨማሪ የዘመናዊ ህክምና ተቋም በቅርበት እንዲኖር የሚያደርግ ነው።

ከግንባታው ገንዘብ 80 በመቶ የሚሆነው ከአሜሪካ ዩሰድ የተገኘ ሲሆን ቀሪው ከሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች መገኘቱንም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የተጨማሪ ሆስፒታል ግንባታ በርካታ ገንዘብ ተመድቦ በዘመናዊ አሰራር የሚሰራ በመሆኑ በታቀደው ጊዜ ገደብ በጥራት እንዲጠናቀቅ ክትትልና ቁጥጥር በትኩረት እንደሚያደርጉ የሆስፒታሉ ግንባታዎች መሐንዲስ የሆኑ እንጂኔር በፀጋው መለሰ ተናግረዋል።

በቦታው የሶዶ ከተማ ከንቲባ ወክለው የተገኙ የከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍስሃ ፀጋዬ እንደገለፁት ሆስፒታሉ በየጊዜው የህክምና አገልግሎትን ለማሻሻልና ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት በማድነቅ ለስራው ስኬታማነት የከተማ አስተዳዳሩ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የዎላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል በሚሰጠው ህክምና አገልግሎቶች ከአፍሪካ ከሚገኙ አስር ሆስፒታሎች መካከል አንዱ ሲሆን በዛሬው ዕለት የተጀመረው ተጨማሪ ግንባታ ሲያልቅ እንዲሁም ዘመናዊ የህክምና መሣሪያዎች አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ በሀገሪቱ ጤና አገልግሎት ዘርፍ የራሱን ሚና ለመጫወት መታቀዱንም ከሆስፒታሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።