ዩኒቨርሲቲው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከዩኒቨርሲቲው ሰራተኖች እና ከውስጥ ገቢ በጀት ያሰባሰበውን 39 ሚሊዮን ጥሬ ብር እና 6.5 ሚሊየን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት አስረክቧል።

በመረሃግብሩ ላይ ተገኝተው ለተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎች ገለጻ ያደረጉት የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ፤ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በመጀመሪያው ዙር የድጋፍ አሰባሰብ መርሃ ግብር ለመከላከያ ሰራዊት የ 2 ሚሊየን ጥሬ ብር እና 100 ኩንታል ንጹህ ጤፍ መለገሱን ገልጸዋል።

በሁለተኛው ዙር የድጋፍ ማሰባሰብ ጥሪም የዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ሠራተኞች የሀገር ውስጥና የውጭ ጠላትን በጋራ ለመመከት የቀረበላቸውን ሀገራዊ የውግንናና የደጀን ጥሪ በመቀበል የአንድ ወር ደወወዛቸውን 37 ሚሊየን ብር፤ የዩኒቨርሲቲው አተዳደርም ከውስጥ ገቢ 2 ሚሊየን ብር፤ በድምሩ 39 ሚሊየን ብር ማበርከት መቻላቸውን ጠቁማዋል።

“በሀገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተልኳቸውን ማሳካት የሚችሉት ሀገር ህልውናውን ጠብቆ ሲኖር ነው። ሕዝቦችም ህልውናቸው የሚረጋገጠው።ሀገር አፍራሽ አሉታዊ ሀሳብና ድርጊትን በማውገዝ ሰፊ ስራ ሰርተናል። ይኸው ተግባር ተከታታይነት ባለው ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ ፕ/ር ታከለ ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከፍ እንድትል ብዙ እንሰራለን፤ ከዚህ ቀደም በተቋም ደረጃ የተካሄዱ የደም ልገሳ መርሃ ግብሮችን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የተጠናከረ የአጋርነት ስራ መስራት አለበት ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፤ የሀሰት ፕሮፖጋንዳን በማክሰን ብሎም እንደ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር፣ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን ውጤታማ ከማድርግ ባሻገር፤ የሀገር መከላከያን የመደገፉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ፕ/ር ታከለ ጠቁመዋል።

ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በተሰማራበት የስራ መስክ ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ በመስጠት፣ አካባቢውን በመጠበቅ፣ እንዲሁም ወደ ጦር ግንባር በመዝመት ጭምር የተጠናከረ ስራ መሰራት አለበት ብለዋል ፕ/ር ታከለ ታደሰ።

“ኢትዮጵያ በሁሉም መድረክ ታሸንፋለች፤ የውስጥ ባንዳዎች እና የውጭ ጠላቶቻችን ያፍራሉ፤ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር እና መላው ሰራተኛም ምንም ጊዜም ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ጋር ይቆማል” ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

በዛሬው እለት በተካሄደ የድጋፍ ርክክብ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ማርታ ሉጂ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ስለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይም ለህልውና ዘመቻው የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያስተምሯቸውን ተማሪዎች ልዩነቶቻቸውን አጥብበው፥ ሀገራዊ አንድነት ላይ የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የማድረግ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲያስቀጥሉም ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ግንባር በመዝመት፣ ስንቅ በማዘጋጀት እንዲሁም አካባቢንው በመጠበቅ እያደረገ ያለው ርብርብ የተከፈተብን ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በድል እንደሚጠናቀቅ አመላካች መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸው፤ የጠላትን የመከፋፈል ስልት እና የሀሰት ፕሮፖጋንዳን በመመከት የሀገርን ህልውና እናስከብር ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር በዛሬው እለት ለሁለተኛ ዙር ባካሄደው ድጋፍ 39 ሚሊየን ጥሪ ብር እንዲሁም በዓይነት ድጋፍ በቁጥር 40 ሰንጋ በሬ፣ 100 ኩንታል ንጹህ ጤፍ፣ 100 ኩንታል ስኳር፣ በቁጥር 50 አልጋ እንዲሁም በቁጥር 200 ብርድ ልብስ ለሀገር መከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ርክክብ አድርጓል።

እንደ ዩንቨርስቲው ኮዳ ዘገባ አስተዳደሩ በጥቅሉ 45 ሚሊየን 500 ሺህ ብር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት በብርና በዓይነት በዛሬው እለት ገቢ ያደረገ ሲሆን፤ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አሳውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: