የዎላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ተሾመ መና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መተግበር ሀገር ለማፍረስ ለሚንቀሳቀሱ አካላት ምቹ ሁኔታ የማይፈጥር በመሆኑ ተገቢና ተግባራዊ የማደርገው ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡ ውስጥ ተደብቀው ድብቅ አጀንዳቸውን ማራመድ የሚፈልጉ ወንጀለኞችን ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት አቶ ተሾመ እነዚህን ለማጋለጥ የሚረዳ በመሆኑ አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ ሀገሬን አድናለሁ ሲሉ ተናግረዋል።
ሀገሪቱ የገጠማትን ከሀዲና ወራሪ ቡድን ድል እስከምታደርግ ድረስ ለየትኛውም መንግስታዊ መመሪያዎች ታዛዥ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አያይዘውም በአካባቢያቸው የሚገኙ የንግድ ቦታዎች ከተጣለው የሰዓት ገደብ አልፈው ሲሰሩ ጥቆማ እንደሚያደርጉም አስረድተዋል።
ባለሶስት እግር አሽከርካሪ ወጣት በፍቃዱ አየለ በበኩላቸው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተጣለው የሰዓት ገደብ ባለማወቅ የወንጀል ተባባሪ ከመሆን የሚያድን መሆኑን ነው የተናገሩት።
በከተማው ውስጥ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ግለሰቦች የተለያዩ ወንጀሎች እንደሚፈፅሙ ተናግረው በአዋጁ የተቀመጠው የሰዓት ማሻሻያ ወንጀል እንዳይስፋፋ ይረዳልም ብለዋል።
በዚህ ሀገሪቱ የመኖርና አለመኖር ስጋት በገጠማት ወቅት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነገሩ ማናቸውም ህግና መመሪያዎች በመተግበር ለሀገር ደጀን እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዋና አስተባባሪ አቶ ብሩክ ሆንጃ አዋጁ የሀገሪቱን ህገመንግስት በመናድ ሀገርን ለማፍረስ ከጠላት ጋር የሚያብሩ ግለሰቦችን ለመለየት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ ቡድኖች ዓላማቸውን የሚያስኬዱት ከሰላማዊ የህብረተሰብ ክፍል ጋር ተመሳስለው በመቅረብ በመሆኑ የድርጊቱን ፈፃሚዎች መንጥሮ ለማውጣት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
በከተማው የጦር መሳሪያ ምዝገባ፣ የአከራይና ተከራይ ምዝገባ እንዲሁም ድንገተኛ ፍተሻ መቀጠሉን ገልፀው ኮሚቴው በየዕለቱ ግብረመልስ የመገምገም ስራ አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
ሀገር አሳልፎ ለመስጠት በድብቅ የሚንቀሳቀሱና አሸባሪውን ቡድን ግልጽ በሆነ መንገድ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት በክትትልና በጥቆማ ተይዘው የምርመራ ሂደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
