በዎላይታ ዞን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ እየተገነባ የሚገኘው የወይቦ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከ12 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገለፀ፡፡

በዞኑ በወይቦ ወንዝ ላይ በ2.44 ቢሊዮን ብር የሚገነባው የወይቦ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ሕዳር 2014 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ከ2-3 ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል፡፡

ፕሮጀክቱ የሚገኝበት ቦታ ዎላይታ ዞን አስተዳደር ሲሆን ግድቡ የሚገነባው በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ እንዲሁም የመስኖ መሰረተ ልማቱ በቦሎሶ ሶሬ ወረዳና በቦሎሶ ቦምቤ ወረዳዎች ውስጥ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ 4 ቀበሌዎችና በቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ 7 ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ ከ20,000 በላይ አርሶ አደሮችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

ፕሮጀክቱ በሁለት ሎቶች ተከፍሎ የሚገነባ ሲሆን ሎት-1 (የግድብና ተያያዥ ሥራዎች ግንባታ) በደቡብ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት እንዲሁም ሎት-2 (የመስኖ መሬት ዝግጅት ግንባታ) የሚገነባው ክሮስ ላንድ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ጋር በጆይንት ቬንቸር በመቀናጀት ነው፡፡

የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መኃንዲስ የደቡብ ዲዛይንና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡

የወይቦ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የግድቡ ርዝመት 660 ሜትርና የግድቡ ከፍታ 32.7 ሜትር ሲሆን 630 ሄክታር ላይ ውሃው ወደ ኃላ የሚተኛ ሲሆን በዚህም ለቱሪስት መስህብነትና ለዓሳ ምርት ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 60 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በመያዝ 3,429 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው ተብሏል።