በጋሞ ምዕራብ አባያ ወረዳ ብርብር ከተማ ነዋሪ የሆነዉ ተከሰሽ ከሪፍት ቫሊ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ በክልኒካል ነርስ ዲፕሎማ፣በደረጃ 4 የክሊኒካል ነርሰ የብቃት ማረጋገጫ እና ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የሙያ ምዝገባ ፈቃድ መረጃ የተሰጠው በማስመሰል በስሙ የመጀመሪያ ደረጃ ክልኒክ ከፍቶ አገልግሎት  ሲሰጥ ተደርሶበታል።

ተከሳሹ ግለሰብ በክሊኒኩ ለመጀመሪያ ደረጃ ያልተፈቀዱ የህክምና ቁሳቁስ እና የተለያዩ  መድሃኒቶች ተገኝተዋል።

ተከሳሹ የፈፀመው ወንጀል በሰዉ እና በሰነድ ማስረጃዎች ተረጋግጦ መዝገቡ ለጋሞ ዞን የሙስና ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ቀርቧል።

በዐቃቤ ሕግ የቀረቡለትን ማስረጃዎች በጥልቀት የተመለከተው የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ህዳር 28/2014 ዓ.ም በዋለዉ  የወንጀል ችሎት ተከሳሽ በ5 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ3 ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኗል።

የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ዘገባ እንደሚያመለክተው በጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ድቪዥን ኃላፊ ም/ኢንስፔክተር ዉብሸት መኮንን ሕብረተሰቡ በተለያዩ መልኮች የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ከፖሊስ ጋር ያለውን ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ  አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።