በመድረኩ የተገኙት የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲርቲ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ ለተማሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት እጅ ለእጅ ተያይዘን ሀገራችን የገጠማትን ፈተና ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም በቀጣይ የሚሰሩ ተግባራትን አስመልክተው ሲናገሩ፤ አመራርና አስተዳደር አካባቢ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን፤ ለተማሪዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ዕቅድ ይዘናል ሲሉም ተናግረዋል።
የተማሪዎች አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እቅድ መያዙን ፕሬዝዳንቱ ገልፀው፤ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በስፋት ለመስራት ታቅዷልም ብለዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ላብራቶሪዎችና ወርክሾፖች 24 ሰዓት እንዲሰሩ ዕቅድ መያዙን ፕሮፌሰር ታከለ ገልፀው፤ የመምህራን ልማትን በማጠናከር ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የሰው ኃይልን ለማፍራት በስፋት እንሰራለን ሲሉም ገልፀዋል።
ለትምህርት ጥራት እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶችን ለይቶ በመፍታት ለተቋም እድገት በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ ርብርብ ማድረግ ከሁሉ ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል፡፡
መልካም አስተዳደርን የማስፈንና ሌብነትን የመከላከል ስራ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ለመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት በመሆኑ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ለተቋም ደህንነት እንሰራለን ብለዋል፡፡
ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲረጋገጥ እና ኢትዮጵያዊነት እንዲያብብ በትብብር እንሰራለን ያሉት ፕሮፌሰር ታከለ፤ በቀጣይ ጊዜያት ስብዕና ግንባታ ላይ በስፋት ይሰራል ሲሉ አውስተዋል።
በዩኒቨርሲቲው ግቢ ጸጉር አንጨባሮ መንቀሳቀስም ሆነ ሥነ-ምግባር የሌለው አለባበስ ተቀባይነት እንደሌለውም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ዴአ የዝግጅት ምዕራፍ አጠናቅቀን የመማር ማስተማር ሥራው በሚፈለገው አግባብ እንዲቀጥል ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ጠንካራ አደረጃት በመመስረት፤ በላብራቶሪ፣ በወርክሾፕ እና በቤተ መጽሐፍት ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜያችውን እንዲያሳልፉ አሳስበዋል፡፡
ከትምህርት ገበታ ላይ የሚቀር ተማሪ ካላ ተገቢነት ያለው አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠቁመው፤ ተማሪዎች የማንበብ ልምዳቸውን በማጠናከር ለውጤታማነት መሥራት እንዳለባቸው ሲሉም ዶ/ር ሙላቱ ተናግረዋል፡፡
አስፈላጊውን ግብዓት የማሟላት ስራ፣ ኮርሶች በተገቢው ማለቃቸውን የመከታተል፣ ለዚሁም ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ የማድረግ እንዲሁም የተማሪ ዲሲፕሊን ተጠብቆ የመማር ማስተማር ስራው ውጤታማ እንዲሆን በተቀናጀ መልኩ እንሰራለን ሲሉም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር አብርሃም ቦሻ ለ2014 የትምህርት ዘመን አስፈላጊውን ዝግጅት መደረጉን ገልፀው፤ በሀገራችን ዘላቂ ለውጥ እንዲመጣ አብረን በትብብር እንሰራለን ብለዋል።
ተቋም እንዳይረበሽ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ያለአንዳች ኮሽታ የመማር ማስተማር ስራው እንዲረጋገጥ በትብብር መሥራት ተገቢ መሆኑን ዶ/ር አብርሃም ጠቁመው ለተማሪዎች አገልግሎት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች የማሟላት ስራ መከናወኑን፣ አገልግሎቶችን በማሻሻል እና በማዘመን ተማሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገው አገልግሎትን እንዲያገኙም መክረዋል።
የዲስፕሊን ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ ያለመሆኑንና ለዚሁም ተገቢነት ያላቸውን የአሰራር መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ለተቋም ደህንነት መረጋገጥ አበክረን እንሰራለን ብለዋል ምክትል ምፕሬዘረዳንቱ፡፡
በዩኒቨርሲቲው ሬጅስትራልና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መ/ር ሳሙኤል ሳርካ የ2014 ዓመታዊ አካዳሚክ ካላንደር በመድረኩ ቀርቧል፡፡
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ምሽት ወደ ግቢ መግቢያ 2:00 እንዲሁም መውጫ ሰዓት ከንጋቱ 12:00 እንዲሆን በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ተወስኗል ሲል የዩንቨርስቲው ኮሙኒኬሽን ዳይረክቶሬት ዘግቧል።