አሸባሪው ሕወሓት በደሴ ፋና ኤፍ ኤም ማሰራጫ ጣቢያ ላይ መጠነ ሰፊ ውድመትና ዘረፋ እንደፈፀመበት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቋል፡፡
በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የደሴ ፋና ኤፍ ኤም ሥራ አስኪያጅ ዘሩ ከፈለኝ እንደገለጹት አሸባሪው እና ወራሪው ሕወሓት ከተማዋን በወረራ ይዞ በቆየበት ጊዜ ለሕዝብ ልሳን የሆኑ የመገናኛ ብዙኃን መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድማት አድርሷል፡፡
መዳረሻውን ጥፋት አድርጎ በየደረሰበት ሁሉ ሰይጣናዊ ተግባሩን እያሳየ የሚገኘው የሽብር ቡድኑ ደሴ በሚገኘው ፋና ኤፍ ኤም የራዲዮ ማሰራጫ ጣቢያ ላይም መጠነ ሰፊ ውድመትና ዘረፋ ፈጽሟል ነው ያሉት፡፡
ጣቢያው ከፊል ሰሜን ሸዋን፣ አፋር እና ምስራቅ አማራ አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ወቅታዊ መረጃዎችን እንደሚያሰራጭ ነው ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡
አሸባሪው ቡድን ባደረሰው ውድመት ተቋሙን ከጥቅም ውጭ ከማድረጉም ባለፈ ዕቃዎቹን ለመተካት በአገር ውስጥ መገኘት የማይችሉ እና ውድ በመሆናቸው ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡
የክልል ጣቢያዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ሰለሞን ገመዳ በበኩላቸው የወደሙ ዕቃዎችን በሚቻለው ፍጥነት አስተካክሎ ጣቢያው ወደ ቀደመ ስራው እንዲመለስ እና መረጃዎችን ለማኅበሰረቡ ተደራሽ እንዲያደርግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ሕወሓት በደሴ ቆይታው በከተማዋ በሚገኙ ሌሎች የመረጃ ምንጭ ተቋማት ላይ ተመሳሳይ ውድመት ማድረሱንም ኮርፖሬቱ አስታውቋል፡፡
