ዋና አስተዳዳሪው በዓሉን በማስመልከት በገለጹት የደስታ መግለጫ በዓሉ ጌታችንና መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ወደ ምድር የመጣበትና ለሰው ልጆች ታላቅ የምስራች የተበሰረበት በዓል በመሆኑ ለመላው የዎላይታ ሕዝብ እና ለክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን በሰላም አደረሳችሁ በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው ህብረተሰቡ ለሰው ልጅ ደስታ መነሻና መድረሻ የሆነውን የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ደስታውን ሲያጣጥም አቅሙ በፈቀደው መጠን አቅመ ደካሞችን በመደገፍ በዓሉን በአብሮነት እንዲያከብር ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በሀገር ህልውና ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመመከት ወደግንባር ለዘመቱ ለጀግና የወላይታ አብራክ ልጆች ቤተሰቦች ሁሉም አካላት ካለው በማካፈል በዓሉን በፍቅርና በአንድነት እንዲያከብሩ በአጽኖት አሳስበዋል ዋና አስተባባሪው፡፡

ለሀገር ሉአላዊነት የህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ላሉ ዘማች ቤተሰቦች ፍቅርና ክብር በማሳየት በዓሉን በጋራ እንደማክበር የሚያስደስት ነገር ስለማይኖር ሁሉም የበዓሉ ቤተሰብ የሆነ የዞኑ ህብረተሰብ ለጀግኖቹ ቤተሰብ አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት በዓሉን በጋራ እንዲያከብር በየደረጃው ያሉ አመራር አካላት እንዲያስተባብሩ አክለው አሳስበዋል፡፡

ወቅቱ ከፍተኛ ነፋስ የሚነፍስበት በመሆኑ ከበዓሉ አከባበር ጋር ተያይዞ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት እሳት በሚነድበት አካባቢ ጥንቃቄ በማድረግ ህብረተሰቡ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ሊከላከል ይገባል ብለዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም ሰሞኑን በስፋት በተከሰተው ጉንፋን መሰል ወረርሽ ላይ የጤና ሚኒስቴር ባካሄደው የናሙና ምርመራ ውጤቱ በብዛት የኮቪድ ቫይረስ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ጠቁመው ህብረተሰቡ በበዓሉ ወቅት በሚደረገው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እና በሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች የኮቪድ መከላከያ ፕሮቶኮሎችን ሳይዘናጋ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው በዓሉ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ጥላቻና ጥርጣሬ ተወግዶ ፍቅርና ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን ያላቸውን መልካም ምኞት በድጋም ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *