የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ለ2014 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት (የገና በዓል) በሰላም አደረሳችሁ በማለት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ በውስብስብ እና ተደራራቢ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ ወደ ትንሣኤዋ እያመራች ባለችበት ወቅት ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህን የገና በዓል ማክበሩ በዓሉን እጅግ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ገለጸዋል።
ኢትዮጵያ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የሚገጥሟትን ፈተናዎች በጽናት ታግላ ገናናነቷን ስታንጸባርቅ የቆየች ታላቅ ሀገር መሆኗን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በአብሮነትና በአንድነት በመስራት ማንኛውንም ችግር መቋቋምና ውጤታማ መሆን ይቻላልም ሲሉ ለሕዝበ ክርስትያኑ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ መላው የሀገሪቱ ሕዝብ እጅ ለእጅ ተያይዞ በመስራት እንዲሁም ሙሉ ትኩረቱን ሰብስቦ የሚያጋጥሙ ማንኛውንም ፈተናዎች በመጋፈጥ የኢትዮጵያን ትንሳዔ ከፍ ለማድረግ ከምን ግዜውም በላይ መስራት ተገቢ ነውም ብለዋል።
በኢትዮጵያ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ሕዝበ ክርስትያኑ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ሰላምና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማስከበር ሲሉ ዝናብና ጸሐይ ሳይበግራቸው በተለያዩ ግንባሮች ላይ ተሰማርተው የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙ የሠራዊት አባላት ፕሮፌሰር ታከለ መልካም ምኞታቸውንም ገልፀዋል።
በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በርካቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ እና ንብረታቸውም የወደመ መሆኑን ፕ/ር ታከለ ገልጸው፤ የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተጠናከረ ስራ ሊሰራ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የሚደረገው ሁሉ አቀፍ ርብርብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህዝበ ክርስትያኑ ይበልጥ ተቀራርቦ መስራት አለበት ያሉት ፕ/ር ታከለ፤ የገና በዓልም የደስታ፣ የአብሮነት፣ የፍቅር እና የአብሮነት እንደመሆኑ በአሉን በመደጋገፍ ልናከብረው ይገባልም ብለዋል።
አውደ ዓመት ለኢትዮጵያውያን የአብሮነት መገለጫ፣ መጠያየቂያ ፣ያለን ተካፍሎ ማሳለፊያ፣ ደስታም ሆነ መዓድ መጋሪያ ቀን መሆኑን ፕ/ር ታከለ ገልጸው፤ በአሉን ስናከብር ከተረፈን ሳይሆን ከዋናችን ቀንሰን ድጋፍ ለሚሹ አካላት ሁሉ ልንደርስላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመጨረሻም በዓሉ ለኢትዮጵያዊያን የብልጽግና፣ የደስታ፣ የሠላምና የአንድነት እንዲሆን ፕ/ር ታከለ ታደሰ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
