እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን ደስ አልን !

የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥረት ውጤት የሆነው አባይ ግድብ በዛሬው ዕለት በይፋ ፍሬ መስጠት ጀመረ።

የዕኛነት ተምሳል፣ የአንድነት ማስተሳሰሪያ ገመድ የሕብረ ብሔራዊ ካባ፣ የጋራ ታሪክ ዐሻራና ማህተም፣ ከግድብም በላይ የትውልድ ጎምቱ ሐውልት ነው – ዓባይ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዛሬ የመጀመሪያውን ኃይል ማመንጨት ጀምሯል።

የቅድመ ኃይል ማመንጫ (early generation unit) በፈረንሳዩ አልስቶን ፍራንስ ኩባንያ እየተገነባ ነው።

6 ሺህ 696 ኪሎ ሜትር የሚዘረጋውና 2 ሺህ 700 ሜትር ኪዩብ በሰከንድ ይወነጨፋል የሚባልለት ዓባይ አሁን ላይ ግስጋሴውን ገታ አድርጎ ወደ ውስጥ በአትኩሮት እንዲያጤን ተደርጓል፤ በሀገር እጅ ለሀገር ልጅ እንዲሆንም ተደርጓል።

አሁን በጉባ ሰማይ ስር ሌላ ብርቱ የታሪክ ምዕራፍ ጅማሮ ሆኗል። መጋቢት 24/2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠው ግድቡ የውኃ ማንደርደሪያ (spiral)፣ የሲቪል፣ ኤሌክትሮ ሜካኒካል፣ የብረታብረት ገጠማና የኃይል መቀበያና ማሰራጫ ጣቢያ ሥራዎቹ በ7 ተቋራጮች እየተከናወኑ ነው።

10 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ጥቅጥቅ የአርማታ ሙሌት የሚፈልገው ዋናው ግድብ በጥሩ ሂደት ላይ ይገኛል። 14 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የዓለት ሙሌት የሚፈጀው የኮርቻ ግድብ ተጠናቋል። ይህም 50 ሜትር ቁመትና 5 ሺህ 200 ሜትር ርዝማኔ አለው።

የግንባታ ሂደቱ ሲጠናቀቅ 246 ኪሎ ሜትር ወይንም ከአዲስ አበባ ሻሸመኔ የሚሆን ርዝመት ወደ ኋላ የሚዘረጋው ሐይቁ የወደፊት ትልቁ ተስፋው እንዳለ ሆኖ በአንደኛና ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌቱም ላብ ያጠመቃቸውን የጉባ ተራሮች ጭምር አረስርሶ እስትንፋስ ለግሷል።

ሁለተኛው የኃይል ማመንጫም በቅርቡ ይጠናቀቃል።

እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን ደስ አልን 