16479658943671629436718266685008

በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ውስጥ በሚገኙ በ157 የከተማ አስተዳደሮችና የወረዳ ማዕከላት ከ65 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ ነገ መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓመተ ምህረት ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል እንደገለፁት፤ የህብረተሰብ አቀፍ የውይይት መድረኩ ዓላማ ጉባኤው በመከረባቸዉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ህዝቡ ግልጽነት እንዲፈጥርባቸው፣ በአስተያቱም እንዲያዳብራቸዉ እንዲሁም ለተፈፃሚነታቸው የነቃ ተሣትፎ ያደርግ ዘንድ አስቻይ ሁኔታን መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው።

የብልጽግና ትልሞች ሊሳኩ የሚችሉት ሁሉአቀፍ የነቃ የህዝብ ተሣትፎ ሲረጋገጥ መሆኑን ያስገነዘቡት ኃላፊዉ ፤ ፓርቲው በጉባኤው ላስተላለፋቸው ውሳኔዎች ወደ ተግባርና ውጤት መሸጋገር የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት የውይይት መድረኮቹ መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል ።

ህብረተሰብ አቀፍ የውይይት መድረኩ የየአካባቢው የህዝብ ጥያቄዎች በህዝቡ ሁሉ አቀፍ ተሣትፎ ይፈቱ ዘንድ የጋራ አረዳድና ዝግጁነት መፍጠሪያ ነዉም ብለዋል።

በመድረኮቹ የህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት የህይወት ፈተና የሆኑ በተለይም የኑሮ ውድነት፣ የሥራ አጥነት፣ የሌብነትና የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል ፣ ፅንፈኝነት ፣ የሠላምና መረጋጋት እጦት እንዲሁም በመሰል ችግሮች መንስዔና መፍትሄ ላይ በመምከር ችግሮቹን በላቀ የህዝብ ተሳትፎና በተቀናጀ መንገድ ለማቃለል መግባባት ላይ እንደሚደረስ አቶ ስንታየሁ አሳዉቀዋል።

በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ የመፍትሄ አቅጣጫና ዕቅድ ታግዞ የጋራና የየድርሻ ርብርብ ለማድረግም መድረኩ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል ።

በአጠቃላይ የህዝብ ዉይይት መድረኮቹ ወሣኝ የሆነውን ህዝባዊ አቅም በተደራጀ አግባብ በማንቀሳቀስ ፈተናዎችን ለመሻገር አጋዥ መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል ፡፡