
አዲስ እየተሰራ ባለ የህንፃ ግንባታ ውስጥ ቀልዳቸው ወደ ፀብ አምርቶ የጓደኛውን ሕይወት በፌሮ ብረት የቀጠፈው ተከሳሽ በፅኑ እስራት እንዲቀጣና ከህዝባዊ መብቶች እንዲታገድ ተወስኖበታል።
በየነ ዮቴ የተባለው የ18 ዓመቱ ወጣት ግንቦት 20/2012 ዓ.ም ከቀኑ 9፡30 ሰዓት ከጓደኛው ሟች አለማየሁ መገኔ ጋር በቦሌ ክፍለ ከተማ አዲስ እየተሰራ ባለ የህንፃ ግንባታ ውስጥ በጉልበት ሰራተኝነት ተቀጥረው እየሰሩ ባሉበት ህንጻ ውስጥ ውስጥ ነው ድርጊቱ የተፈጸመው።
ተከሳሽ ሟችን ለምን ፀያፍ ስድብ ትሰድበኛለህ በማለት ለህንፃ ግንባታ የሚውል የፌሮ ብረት በማንሳት ጭንቅላቱን የመታው ሲሆን ሟችም በራስ ቅሉ ላይ በደረሰ የአጥንት ስብራት በህክምና ቢረዳም ሳይተርፍ ቀርቶ ሕይወቱ ልታልፍ ችላለች።
ተከሳሽም፥ ” ከሟች ጋር የምንዋደድ ጓደኛሞች ነበርን የተጎዳሁት እኔ ነኝ ወንጀሉንም ፈፅሚያለሁ በድርጊቴም ተፀፀቻለሁ“ ሲል በእምነት ቃሉን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርቦ ሰጥቷል።
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ የሌለበት߹ የቤተሰብ አስተዳዳሪ߹የደም ብዛትና የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ህመምተኛ መሆኑ ߹ በማረሚያ ቤት ቆይታው የሰላም ኮሚቴ ሆኖ ማገልገሉ በሃገራዊ የልማት ስራዎች ተሳታፊ መሆኑን በቀረቡት ማስረጃዎች በማረጋገጡ አምስት የቅጣት ማቅለያዎችን በመያዝ ተከሳሽ በ10 ዓመት ፅኑ እስራት አንዲቀጣና ለ4 ዓመት ደግሞ እንደ ምርጫ መሳተፍ ከመሳሰሉ ህዝባዊ መብቶች እንዲታገድ ወስኖበታል።መረጃው የፍትህ ሚኒስቴር ነው።