የፕሬዚዳንት ፑቲን ስልጣን የሚወሰነው በመረጧቸው ሩስያውያን እንጂ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አይደለም ሲሉ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ተናገረዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በፖላንድ ከዩክሬን ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ውይይት፥ ፑቲን በስልጣን ላይ መቆየት የለባቸውም ማለታቸውን ተከትሎ ነው ክሬምሊን ይህን ምላሽ የሰጠችው፡፡

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ፕሬዚዳንት ፑቲን በስልጣን የሚቆዩት ወይም የሚወርዱት በባይደን በጎ ፈቃድና አስተያየት ሳይሆን በመረጣቸው የሩስያ ሕዝብ ውሳኔ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

“በዩክሬን ላይ ያካሄዱት ወረራ የፑቲን የመወሰን አቅም ደካማ መሆኑን የሚያሳይ ነው” ያሉት ፕሬዚዳንት ባይደን፥ በሩስያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ላይ የሚያደርጉትን ውረፋና የማጣጥል ዘመቻ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

ቀደም ሲል ፕሬዚዳንት ባይደን “ፑቲን የጦር ወንጀለኛ ናቸው” ማለታቸውን ተከትሎ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ በሰጡት ምላሽ፥ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የገደለች እና ሀገራትን የወረረች አሜሪካ ፑቲንን የጦር ወንጀለኛ የማለት ሞራል የላትም ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወራትን ባስቆጠረው ሩስያ-ዩክሬን ጦርነት፥ ሩስያ ወታደራዊ ዘመቻዋን አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን የምዕራብ ዩክሬኗን ከተማ ሊዩቭን በሮኬት መደብደቧ ተነግሯል፡፡

የሩስያ ኃይሎች የኒውክሌር ጣቢያ ሰራተኞች የሚኖሩባትን ስላቫቲች ከተማን እንደተቆጣጠሩ የሩስያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ ገልጸዋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው፥ ወረራውን ለመግታት ምዕራባውያን የወታደራዊ ጦር መሳሪያዎችን ብቻ ሳይሆን መገጣጠሚያዎችን ጭምር እንዲልኩላቸው ጠይቀዋል፡፡ ባሁኑ ወቅትም የዩክሬን ወታደሮች በዋና ከተማዋ ኪየቭ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች በሰፈሩ የሩስያ ወታደራዊ ኃይሎች ላይ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትሬስ ደግሞ ሞስኮ ሙሉ በሙሉ የተኩስ አቁም ስምምነት ካደረገች እና ወታደሮቿን ጠቅልላ ከዩክሬን የምታስወጣ ከሆነ ዩናይትድ ኪንግደም በሩስያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ልታነሳ ትችላለች ነው ያሉት፡፡

ከተጀመረ 32 ቀናትን ያስቆጠረው የሩስያ-ዩክሬን ጦርነት፥ 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች ከዩክሬን እንዲሰደዱ ማድረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡ 6 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ደግሞ አንፃራዊ ሰላም ወዳለባቸው የዩክሬን አካባቢዎች የፈለሱ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸው ነው የተገለፀው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: