
በዳውሮ ዞን በዛባ ጋዞ ወረዳና በለሎች አከባቢዎች የተከሰተውን የምግብ እጥረት ችግር ለመቅረፍ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ ቀረበ።
የዳውሮ ዞን አደጋ ስጋት አመራር ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ዋሰሁን አባተ በዞኑ በዛባ ጋዞ ወረዳና በለሎች አከባቢዎች የተከሰተውን የምግብ እጥረት ችግርና የእንስሳት ሞት ለመቅረፍ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል ።

የዞኑ የአደጋ ስጋት አመራር ፅ/ቤት ከዞን አስተዳደርና ከለሎች የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አብይና ንዑሳን ኮሚቴ በማቋቋም ለአደጋው ምላሽ ለመሰጠት ወደ ትግበራ መግባቱን የገለፁ አቶ ዋሰሁን በአከባቢው ለተከሰተው የምግብ እጥረትና ለእንስሳት ሞት ችግር በኡማ ወንዝ በተገነባው የሀይል ማመንጫ ግድብ አማካኝነት በተፈጠረው ሀይቅ ምክንያት የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥና በአከባቢው ለረዥም ጊዜ የተፈጠረ የዝናብ እጥረት ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።
አያይዘውም አቶ ዋሰሁን በአከባቢው ከዚህ በፊት በነባሩ የደቡብ ክልል በልማታዊ ሴፍቲኔት ለቋሚ ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች በማህበራዊ አገለግሎት የሚደረግ ድጋፍና ለህፃናት የሚደረግ የትምህርት ቤት ምገባ አገለግሎት ለ3 ወራት መቋረጡንም ገልፀዋል።
በአደጋው በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት መሞታቸውና በርካታ ህፃናትና እናቶች ለከፋ የምግብ እጥረት ችግር መጋለጣቸው ተገልጧል ።
አቶ ዋሰሁን አደጋው በዞኑ በኡማ ወንዝ ተፋሰስ አከባቢዎች በሆኑ በሎማና በገና ወረዳዎችም የተከሰተ ቢሆንም በተለይ በዛባ ጋዞ ወረዳ በጋራዳ ባጭሪ፣ በጋራዳ እንታላ፣ በዳሻ አጃ እና በለሎች ቀበሌያት እጅግ የከፋ መሆኑን አብራርተዋል።
በዞኑ ለአደጋው ምላሽ ለመስጠት በተቋቋመው ግብረ ሀይል አማካኝነት የተለያዩ የእህል አይነቶች፣ የእንስሳት መድሀኒትና ለህፃናት የሚሆኑ አልሚ ምግቦች ተገዝተው ወደ አከባቢው የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል ።
የቅድመ ምርት ግምገማ መነሻ በማድረግ ችግሩን ለክልልና ለፌደራል የባለድርሻ አካላት ቀደም ብለን አሳውቀናል ያሉት አቶ ዋሰሁን በተለይ አሁን በአከባቢው ያለው ችግር ከፍተኛ ስለሆነ ሁሉም የባለድርሻ አካላት ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በመጨረሻም የዞኑ የአደጋ ስጋት አመራር ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ዋሰሁን የዞኑ አስፈፃሚ አካላት የዞኑን የመንግስት ሰራተኞችን፣ አመራሮችን፣ ነዋሪዎችንና ለሎችን በማስተባበር እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ገልፀው አደጋውን ለመቆጣጠርና ለተጎጂዎች በቂ ድጋፍ ለማድረግ የሁሉም አካል ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘገባው: የዳውሮ ዞን የመን/ኮ/ጉ/መምሪያ ነው።