
የሙስና ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች ከ14 እስከ 3 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን የጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ አስታወቀ
➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖
የመንግሥትንና የህዝብን ሀብት ለግል ጥቅማቸው በማዋል የሙስና ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች ከ14 እስከ 3 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና የገንዘብ መቀጮ ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን የጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ብላቴ አስታውቀዋል።
የጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ በአዋጅ ቀጥር 177/2011 በተዋረድ በተሰጠው ስልጣን መሠረት ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን ብሎም የሕግ የበላይነት ለማስከበር የሚሠራ ተቋም መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።
በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት የተሰጣቸውን ኃላፍነት በሕገወጥ መንገድ ተጠቅመው የመንግስትንና የህዝብ ሀብት ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ የዘርፍ ሥራ ሂደት አስተባባሪና ባለሙያዎች በድምሩ 6 ግለሰቦች ላይ የእስራትና የገንዘብ መቀጮ ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን የመምሪያ ኃላፊ ጠቁመዋል።
በዚሁ መሠረት የሙስና ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች እንደየጥታፋቸው ውሳኔ የተላለፈባቸው ሲሆን፣ 1ኛ ተከሳሽ 14 ዓመት ጽኑ እስራት ከ40 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ፣ 2ኛ ተከሳሽ 13 ዓመት ከ35 ሺህ ብር፣ 3ኛ ተከሳሽ 11 ዓመት ከ40 ሺህ ብር ፣ 4ኛ ተከሳሽ 4 ዓመት ከ20 ሺህ ብር እና ሌሎች ሦስቱ ግለሰቦች እያንዳንዳቸው በ3 ዓመት ጽኑ እስራትና 10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በሣውላ ከተማ አስተዳደር ውሃ አገልግሎት ድርጅት የዳቅሾ፣ የዝርቆ እና የኩስቲ የውሃ ግንባታ ከፋይናንስ ግዥ አዋጅ ውጭ በሆነ መንገድ የ5.3 ሚሊዮን ብር የአከባቢ ጨረታ በማውጣት ተገቢ ያልሆነን አካል በማሳለፍ የሙስና ወንጀል የፈፀሙ የጨረታ ኮሚቴ አባለት፣ የማኔጅመንት አባላት እና ሥራ አስኪያጅ ከ9 ዓመት እስከ 5 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እና እያንዳንዳቸው ከ50,000 እስከ 5,000 ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑ ተገልጿል።
በዚሁ መሠረት 1ኛ ተከሳሽ 9 ዓመት ጽኑ እስራት ከ50,000 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ፣ 2ኛ ተከሳሽ 8 ዓመት ከ50,000 ሺህ ብር፣ 3ኛ ተከሳሽ የፕሮጀክቱ አማካሪ 8 ዓመት ከ50,000 ሺህ ብር እና ሌሎች የማኔጅመንት አካላትና የጨረታ ኮሚቴ አባላት እያንዳንዳቸው 5 ዓመት ከ6 ወር በሚደርስ ጽኑ እስራትና 5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን የመምሪያው ኃላፊ ገልጸዋል።
ከ2013 ዓ.ም የዞረ 14 በ 2014 ዓ.ም አዲስ የቀረበ 28 በድምሩ 42 የሙስና ክስ መዝገብ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ውሳኔ ያገኘ 28 መዝገቦች ላይ ውሳኔ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በዛላ ወረዳ ጋልማ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ሥራ አስኪያጆችና ባለሙያዎች አማካኝነት የሊዝ ሕጉን በሚፃረር መንገድ በሕገወጥ አሠራር ለግለሰቦች የተሰጣቸው 14.52 ሄክታር ወይም 145,200 ካሬ ሜትር ቦታ በሕገ ወጥ የመሬት ወረራ መከላከል ግብረ ሃይል ወደ መሬት ባንክ ተመላሽ እንዲሆን መደረጉን ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተመሳሳይም በዛላ ወረዳ ፋይናንስ ጽህፈት ቤት የሴፍትነት ክፍያ ኦፊሰሮች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሕገወጥ መንገድ በመጠቀም ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከፋይናንስ መመሪያና ደንብ ውጪ በሆነ መንገድ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው በኦዲት ተረጋግጦ፣ በአሁኑ ሰዓት ግለሰቦች በወንጀልና በፍትሐብሔር ሕግ እየተጠየቁ መሆናቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።
እንዲሁም በገዜ ጎፋና ኦይዳ ወረዳዎች 26.023 ሄ/ር መሬት በሕገወጥ መንገድ በግለሰቦች የተያዘው በፍትሐብሔር ክስ ቀርቦባቸው ውሳኔ ተሰጥቶ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ ቦታዎች ወደ መሬት ባንክ መመለሱንም ኃላፊው አክለዋል።
በ2014 ዓ.ም በሴቶች ላይ የተፈጸሙ አስገድዶ መድፈርና ሙከራ እንዲሁም ያለዕድሜ ጋብቻ እና ሌሎች መሰል ወንጀሎች ተፈጽመው ከቀረቡ 181 መዝገብ ውስጥ በ113 መዝገብ ላይ የጥፋትኝነት ውሳኔ መሰጠቱንገልጸው፣ ቀሪ መዝገቦች በፍርድ ሂደት ላይ መሆኑን አቶ ደመላሽ ተናግረዋል።
በሕፃናት ላይ የተፈጸሙ 45 የአስገድዶ መድፈርና ያለዕድሜ ጋብቻ የወንጀል ክስ መዝገቦች በተያዘው በጀት ዓመት በ33 መዝገቦች ላይ ውሳኔ የተሰጠባቸው ሲሆን ቀሪ መዝገቦች በፍርድ ሂደት ላይ መሆናቸውን አቶ ደመላሽ ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ ከ2013 ዓ.ም የዞረ 495 በ2014 ዓ.ም አዲስ የቀረበ መዝገብ 2963 በድምሩ 3408 መዝገብ ውስጥ በዐቃቤ ህግ የተለያየ ሕጋዊ አስተያየትና ውሳኔ ከተሰጣቸው 3324 መዝገብ ውስጥ በ2835 መዝገብ ላይ ክስ ተመሠርተው በ2751 መዛግብት ላይ ውሳኔ መተላለፉንም የመምሪያው ኃላፊ ተናግረዋል።