ዎላይታ ዲቻ መደወላቡና ሙገር ሲሚንቶ በቱነዚያ አስተናጋጅነት ከሚያዚያ 27 እስከ ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም በሚካሄደው 40ኛው የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ይሳተፋሉ።

የአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን በላከው ደብዳቤ ተሳታፊ ክለቦችን እንዲያሳውቅ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

በዚሁ መሰረት መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ፣ ዎላይታ ዲቻና ሙገር ሲሚንቶ በውድድሩ ላይ መሳተፍ የሚያስችላቸውን የመጀመሪያ ዙር ምዝገባ ማካሄዳቸውን ኢዜአ ከኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በነበራቸው ደረጃ አማካኝነት የተለዩት ተሳታፊ ክለቦቹ በውድድሩ መሳተፍ የሚያስችለውን የመጨረሻውን የምዝገባ ሂደትና ተጓዳኝ ጉዳዮች እስከ ሚያዚያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲጨርሱ የአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን የጊዜ ገደብ ማስቀመጡን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሶስቱ ክለብ አመራሮች በውድድሩ ለመሳተፍ የሚጠበቅባቸውን የወረቀት ስራዎች የማሟላት ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዎላይታ ዲቻ ቮሊቦል ክለብ መጋቢት 30 ቀን 2014 ዓ.ም ለአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ዝግጅት ማድረግ እንደሚጀምር አስታውቋል።

ሙገር ሲሚንቶና መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ክለቦችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ዝግጅት እንደሚገቡ ጠቁመዋል።

በ40ኛው የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር 24 ክለቦች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

በቱኒዚያ በተካሄደው 39ኛው የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር የአገሪቷ የቮሊቦል ክለብ ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ ማሸነፉ ይታወሳል።

የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር እ.አ.አ በ1980 የተጀመረ ሲሆን የግብጹ አልሀሊ 14 ጊዜ፣ የቱኒዚያው ሲኤስ ሰፋክሲያን ስድስት እንዲሁም የግብጹ ዛማሌክና የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ በተመሳሳይ አምስት ጊዜ አሸናፊ ሆነውበታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *