ዩኒቨርሲቲውን ከብልሹ አሰራርና ከመልካም አስተዳደር እጦት ለመታደግ ባለፉት ጥቂት አመታት በተሰሩ ስራዎች አዎንታዊ ለውጥ መታየቱ፤ ይህም በሰላምዊ መማር ማስተማር፥ በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር፥ በአሳታፊ የማህበረሰብ አገልግሎት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ስርዓት መስክ ተቋማዊ እምርታ ማሳየቱ በግምገማዊ መድረጉ የተገለጸው።

በመድረኩ የተገኙት የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ተግተው በመስራትና እውቀትን በተግባር በመግለጥ እንደ ተቋም “በ2022 ዓ.ም ቴክኖሎጂ መር የግብርና እና ጤና ልዕቀት ማህከል” ለመሆን የሰነቅነውን ራዕይ ማሳካት አለብን ብለዋል።

ሠላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ገልጸው፤ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ስራን ለማረጋልገጥ እና ለማዝለቅ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን ከአካባቢ እና ከተቋም አውድ አንጻር በመገምገም የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳይፈጠር በተቀናጀ መልኩ መስራት እንደሚገባ ብሎም ብልሹ አሰራርን ከዜሮ በታች ለማድረግ የሚያስችል የአሰራር ስርዓትን መዘርጋር ተገቢ ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ስር የሚገኙ 16 ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሮች በ2014 ዓ.ም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በየዘርፋቸው ያከናወኑት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በማቅረብ፥ በአፈጻጸም ደረጃ በተስተዋሉ ውስንነቶች እና ቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊተገበሩ በሚገቡ ሥራዎች ዙሪያ የስራ አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።

በመድረኩ በዋናነት ለሰላማዊ መማር ማስተማር እና ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ተግዳሮት የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በጥልቀት ተለይተው አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት መከናወን ባለባቸው አበይት ተግባራት ዙሪያ ጥልቅ ውይይትም ተካሂዷል።

በዘርፍ በተካሄደ የ9 ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ የሕዝብ ለሕዝብ የግንኙነት እና የኮሚዩኒኬሽን ተግባርን በማጠናከር የተቋምን በጎ ገጽታ መገንባትና እይታን ከፍ ማድረግ እንደሚገባ፤ በአለም አቀፍ ግንኙነት እና አጋርነት መስክ የተጀመሩ ተግባራትን በማጠናከር ሀብት የማፈላለግ ሥራ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገልጿል።

ሠላምን እና ጸጥታን ከማስካበር ረገድ የምድር ግቢ ጥበቃና ደህንነት ዳይሬክቶሬት በስሩ ያሉትን የሰው ኃይል የፍተሻ ስርዓትን በማጠናከር የሠላም ማስከበር ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፤ ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር እጦትን በተቀናጀ አግባብ መከላከል እና ማስወገድ እንደሚገባ፤ የፍትህ ስርዓትን የሚያዛባ ወንጀል እንዳይበራከት የህግ ማስከበር ስራ ሊጠናከር እና የተቋም ሀብት የማስመለስ ተግባር በጥብቅ ዲስፕሊን መመራት እንዳለበት፤ ተቋማዊ የውል አስተዳደር ስራዎች በህግ አግባብ ተቃኝተው መተግበር እንዳለባቸውና ከኦዲት ግኝት የነጻ ሥራ መሰራት እንዳለበት ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

ከልማት ዕቅድ ዝግጅት፥ ክትትልና ግምገማ ረገድ ፋይናሻል እና ፊስካል ስራዎች በጥልቀት መገምገም እና ሀብት ለታለመለት ዓላማ መዋሉ መፈተሽ እንዳለበት፤ ተቋማዊ መረጃ አስተዳደርና አያያዝን የማዘመን ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ፤ ተቋማዊ የለውጥ ስራዎች የተቋሙን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሊቀርፍ በሚችል መልኩ ሊተገበር እንደሚገባ፤ የስርዓተ ጾታ አካታችነት፥ የአካል ጉዳተኝነትና የኤችአይቪ እና ስነ-ተዋልዶ ጤና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊተገበር እንደሚገባ፤ የትምህርት ጥራት ቁጥጥር ተግባር ከምን ግዜውም የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል።

የዩንቨርሲቲው ኮሙኒኬሽን ዳይሮክቶሬት የላከልን መረጃ እንደሚያመለክተው በግምገማዊ የምክክር መድረኩ ማጠቃለያ ብልሹ አሰራርን በማስወገድና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ሁለንተናዊ ተቋማዊ ለውጥ ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *