

ከደቡብ ኮሪያ የተወጣጡ የጥርስ ስፔሻሊስት ሀኪሞች ልዑክ በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አደረጉ።
ልዑካን ቡድኑ በዩኒቨርሲቲው ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፓታል ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተወጣጡ የጥርስ ህክምና ስፔሻሊቲ ተማሪዎች የጥርስ ተከላና ፕላስቲክ ቀዶ ህክምና በተመለከተ ስልጠና እየሰጡ መሆኑም ተገልጿል።

ለይፋዊ ሥራ ጉብኝት የመጡትን እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ፤ ከዩኒቨርስቲው የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ በጤና ዘርፍ ከሚሰሩ ሥራዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ቡድኑ ለጥርስ ሀኪሞች ስለጥርስ ተከላና ስለፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ስልጠና ለመስጠት መምጣታቸውን አድንቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ ዩኒቨርሲቲው ከኮሪያ መንግስት ጋር በግብርና፣ በሰው ሀብት ልማት፣ በማዕድን ምርት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል።
በሥራ ጉብኝት ወቅት ከደቡብ ኮሪያ የተወጣጡ የጥርስ ስፔሻሊስት ሀኪሞች ልዑካን ቡድን አስተባባሪ ዶ/ር ማቲው ካውን በበኩላቸው፤ የዩኒቨርሲቲውን የሥራ ጉብኝት ግብዣን አድንቀዉ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተለያዩ ጉዳዮች በጋራ ለመሥራት እንስማማለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ የBMW አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዮሴፍ ቶጋ የደቡብ ኮሪያ ልዑካን ቡድኑ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ምርጫቸው አድርገው በዩኒቨርሲቲው ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፓታል ሰለጥርስ ህክምና ስልጠና ለመስጠትና የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ለማድረግ መምጣታቸውን አክለው ገልጸዋል።
በሆስታሉ የጥርስ፣ የፊትና የመንጋጋ ቀዶ ህክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና የአፍ የፊትና የመንጋጋ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት (Ora & Maxillofacial Surgeon) የሆኑት ዶ/ር ልደቱ አፈወርቅ ስልጠናው በሆስፒታሉ ላሉ የጥርስ ሀኪሞችም ሆነ ከሌላ ቦታ ለመጡት አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው፤ በሆስፒታሉ እየተሰጠ ያለው የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ልዩ ልምድ የሚቀሰምበት ነው ብለዋል።

በሆስታሉ እየተሰጠ ያለው ስልጠናና የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑን እንዲሁም የስልጠናው ተሳታፊዎች በጂማ፣ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በወሎ እና ልሎች ዩኒቨርሲቲዎች የአፍ፣ የጥርስ፣ የፊትና የመንጋጋ ህክምና ስፔሻሊቲ ትምህርት እየተከታተሉ ያሉ ተማሪዎች መሆናቸውን ከአስተባባሪዎች ለመረዳት ተችሏል።