መንግስት ብሄርን እና ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሁከት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል

ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ ብዝሃ ባህሎች፣ ታርኮችና ኃይማኖቶች ያሉባት ሀገር ነች።

ብዝሃነታችን በህብረተሰቡ መካከል መቻቻልን፣ መከባበርንና መደጋገፍን አልፎም የህብረ ብሔራዊ አንድነታችን መገለጫ እንጅ ለመገፋፋትና ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ለማድረስ ምክንያት አይሆንም ።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ጥንትም ሆነ ዛሬ በየጊዜው የሚገጥሟትን ፈተናዎች እየተሻገረች ሉዓላዊነቷን አስከብራ ኖራለች።

በነጻነቱ የማይደራደረው የሀገራችን ህዝብ በዘር፣በጎሳ እና በሀይማኖት ሳይከፋፈል ጠላትን እየመከተ ታፍራና ተከብራ የኖረች ሉዓላዊት ሀገር አስረክቦናል።

በህዝቦቿ ደም እና አጥንት የተገነባችን ሀገር ለማፍረስ ጠላት ሌት ተቀን እየተጋ ነው። በግልጽ ጦርነት ከማወጅ ጀምሮ በሁሉም ዘርፍ ረጃጅም እጆቹን እያስገባ ህዝብ እንዲሸበር እና ሀገር እንዳትረጋጋ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጠላቶች የሀገራችንን የእድገት ጉዞ ለማደናቀፍ ሴራ ሸርበው እና ወጥመድ ዘርግተው ያለ የሌለ ሀይላቸውን እየተጠቀሙ ነው።

ሀገር እንዳይረጋጋ በህዝቦች መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር እና ሀገሪቱን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ህዝብ እንዲሸበር በመስራት ላይ ናቸው።

ለሴራቸው ማሳኪያ ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ በሃይማኖት ሽፋን ከውጪ ኃይሎች ጋር በማበር የጥፋት በትራቸውን እያሳረፉ ነው ።

በቅርቡ በክልላችን ስልጤ ዞን የተከሰተው ችግር አንዱ ማሳያ ነው።
ለዘመናት ተቻችለው፣ ተከባብረውና ተደጋግፈው በሚኖሩ ሙስሊምና ክርስትያን ህዝቦች መካከል ፀብ በማጫር በኃይማኖት ሽፋን እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም የገቡ ኃይሎች ሴራ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ማክሸፍ ተችሏል።

መንግስት ብሄርን እና ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሁከት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱት አካላትን በመለየት ለህግ የሚያቀርብ ሲሆን በአጥፊዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል።

መላው የክልላችን ህዝብ በሀይማኖት ተቋማት እና በምዕመናን ላይ እየተሰነዘረ ያለውን ጥቃት በማውገዝ ከዚህ ቀደም የነበረንን የመቻቻል፣የመከባበር እና የአንድነት እሴቶች ማጎልበት ይኖርብናል።

አንድ ስንሆን ጠላቶቻችን ያፍራሉ፣አንድ ስንሆን ጥንካሬያችን ይጎላል፣አንድ ስንሆን የጠላት ሀይል ይዳከማል፣አንድ ስንሆን ወደምንፈልገው እድገት እንሸጋገራለን።

መላው የክልላችን ህዝቦች ከመንግስት ጎን በመሆን ኢትዮጵያን ለማተራመስ ፍላጎት ያላቸውን ሀይሎች እንዲታገሉ የክልሉ መንግስት ጥሪ ያቀርባል።

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1443ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!

በድጋሚ ኢድ ሙባረክ!!

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት

ሚያዝያ 24/2014

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: