1651505919579

በማረቃ ወረዳ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ለተከታታይ ቀናት ከፍተኛ ንፋስና በረዶ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ በንብረት ላይ መጠነኛ ጉዳት ማድረሱን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት አስታውቋል።

ቅዳሜ ምሽት የጣለው ሀይለኛ ነፋስን የቀላቀለው ዝናብ በዋካ 01፣ ዋካ 02 እና ኢየሱስ ቀበሌዎች ላይ በግለሰብ መኖሪያና ንግድ ቦታዎች እና በመንግሥት ንብረቶች ላይ መጠነኛ ጉዳት አድርሷል።

እንዲሁም እሁድ እለት ከሰዓት አሥር ሰዓት አካበቢ ከፍተኛ በረዶን የቀላቀለው ዝናብ በማይዲ ቀበሌ መሀል ካንቂና ዮዮ ንዑስ እና ጉዱሙ ቀበሌ በተወሰኑ አካባቢዎች በአርሶ አደር ሰብልና ንብረት ላይ መጠነኛ ጉዳት ማድረሱን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት አደጋ ስጋት ስራ አመራር ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ብርሀኑ ጉልቱሞ አስታውቀዋል።

አቶ ብርሃኑ አክለው ክስተቱ ብዙም ሳይመሽና በቀን መፈጠሩ የጉዳት መጠኑን መቀነሱን ገልፀው በ5ቱም ቀበሌ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም ግምቱ ለጊዜው በውል ያልታወቀ ቀላል የማይባል ንብረት መውደሙን ገልፀዋል።

ዝናቡ ቀጣይነት ልኖረው ስለሚችል ህብረተሰቡ ግንዛቤ በመዉሰድ እንዲጠነቀቅና እንዲሁም መንግሥትም ቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን በማስተባበር ሊደርስ የሚችለዉን አደጋ መከላከል እንደሚገባ መጠቆሙን ከወረዳው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።