

ቤተክርስቲያን ሰብረው ገንዘብ የዘረፉ ግለሰቦች በሁለት ሙስሊም ወንድማማች እና በአከባቢው ህብረተሰብ ትብብር ለህግ እንዲቀርቡ መደረጋቸውን በጉራጌ ዞን የሶዶ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አስታወቀ።

በሶዶ ወረዳ ጊሚሴ ቀበሌ መድሃኔዓለም ቤተ-ክርስቲያን መስኮት ሰብረው ከሙዳየ ምፅዋት ውስጥ ገንዘብ የሰረቁት ትዛዙ ፍቅሬና አብርሀም ሞላ የተባሉ ግለሰቦች በአቶ በመቅቡል መሀመድ እና በአቶ በሀይሩ መሀመድ እንዲሁም በአካባቢው ማህበረሰብ ትብብር እጅ ከፍንጅ ተይዘው ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉን የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር አለማየሁ ደነቀ ተናግረው ወንጀለኛ አብርሀም ሞላ ከዚህ በፊትም ነጌሳ ስላሴ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የተቀመጠ ጤፍ በመዝረፍ ክስ ቢመሰረትበትም እድሜው አልደረሰም በሚል የተለቀቀ ሲሆን ሁለተኛው ወንጀለኛም ከዚህ ቀደም የማጭበርበር ወንጀሎችን ሲስራ የነበረ ግለሰብ ነው ብለዋል።
ኮማንደሩ አያይዘውም በየአካባቢው የሚታዩ ፀጉረ ልውጦችን መረጃ ለህግ አካል መጠቆምና ተቋማትን በዓግባቡ መጠበቅ እንደሚገባ አስረድተው ወረዳው ላይ ያሉ ሁሉም ሀይማኖቶች ተቻችለው እና ተከባብረው የሚኖሩባት እንደመሆኑ ማህበረሰቡ ከህግ አካል ጋር በመቀናጀት ወንጀለኞችን መያዝና ለፍርድ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ወንጀለኞቹን ከያዙት መካከል የቀበሌው ሚሊሻ አቶ መቅቡል መሀመድ እንደተናገሩት ቤተ-ክርስቲያኑ አካባቢ እርሻ እያረሱ እንደነበርና ቤተ-ክርስቲያኑ ሲንኳኳ ሰምተው ወደ ቀበሌው ኮማንደር ስልክ በመደወል መረጃ እንደሰጡና ኮማንደሩም የይድረሱልኝ ጥሪ በማሰማት በህዝቡና በሚሊሻው ትብብር እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን አስረድተዋል።
አቶ መቅቡል ጨምረው እንዳስረዱት ዘራፊዎቹ አካባቢው ላይ ሲንቀሳቀሱ ፊታቸውን በመሸፈን ሲሆን እኛም ጥርጣሬውስጥ በመግባትና በመከታተል ጥቆማ ያደረግን ሲሆን ወረዳው አካባቢያችንን ከፀጉረ ልውጦች እንድንጠብቅ በተደረገው መሰረት ወጀለኞቹን መያዝ ችለናል ብለዋል።

የወረዳው ቤተ-ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ መዊ አወቀ ወንድሙ በወረዳው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቤተ-ክርስቲያናት እየተሰበሩ ሙዳየ ምፅዋቶች እየተዘረፉ እንደሆነና ዘራፊው ገንዘቡን ሳይሆን የሚፈልገው ህዝቡ ተረጋግቶ እንዳያመልክ ስለሆነ የሚፈለገው መንግስትም ሆነ ማህበረሰቡ የእምነት ተቋማትን መጠበቅና ችግሮች ተፈጥረው ሲገኙ መረጃ ለህግ አካል መስጠት እንደሚያስፈልግ አስረድተው በዛሬው እለትም ሙስሊም ወንደሞቻችን ያደረጉት ተግባር የሚያስመሰግን ነው ብለው በተያዙት ወንጀለኞች ላይም አስተማሪ የሆነ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ መናገራቸውን የዘገበው የሶዶ ወረዳ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።