በሀገራዊ ምክክሩ ቅራኔን ፈትቶ የጋራ መግባባት ለመፍጠር “ጎንዶሯ፣ አዋሲያ እና ጉታራ” የተሰኙ የዎላይታ ቱባ የግጭት አፈታት ዘዴ በዳይና ተበዳይ መካከል ዘላቂ እርቅና ሰላም የሚዘራ በመሆኑ መንግስት መሰል ባህላዊ እሴቶችን መጠቀም እንደሚገባ የዎላይታ የሀገር ሽማግሌዎች አሳስበዋል።

ለግጭት መንስኤ የሆኑ ልዩነቶችን ለማጥበብ የህዝቡን የሰላም ግንባታ እሴቶች ለሀገራዊ ምክክሩ መጠቀም እንደሚገባ የዎላይታ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ገልጿል።

ኢትዮጵያዊያን በየአካባቢው ማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ቱባ ባህሎችን ተጠቅመው ልዩነታቸውን በመፍታት እርቀ ሰላም ማውረድ እንዳለባቸውም የሀገር ሽማግሌዎቹ መክረዋል።

የዎላይታ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ አብርሃም ባቾሬ፤ በዎላይታ ብሔር ህዝብ የሚጠቀምባቸው ሁለት ዓይነት ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች እንዳሉ ተናግረዋል።  

“ጎንዶሯ” የተሰኘው የግጭት አፈታት ዘዴ ከፍተኛ የሚባል ወንጀል የፈፀመ አካል ከበደለው ወገን ጋር የሚሸማገልበት መሆኑን ገልፀዋል።
 
“አዋሲያ” የተባለው የግጭት አፈታት ዘዴ ደግሞ በቤተሰብና ጎረቤት ደረጃ የሚፈጠሩ ቅራኔዎች የሚፈቱበት መንገድ መሆኑን  ተናግረዋል ።

በአሁን ወቅትም እነዚህን የግጭት መፍቻ መንገዶች አጠናክሮ በመጠቀም እርቀ ሰላም የማውረድ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

“በሀገር ደረጃ ለግጭት መንስኤ የሆኑ  ልዩነቶችን ለማጥበብም በየአካባቢው እነዚህንናመሰል ዘላቂ የሰላም ግንባታ እሴቶን ለሀገራዊ ምክክሩ መጠቀም ይገባል” ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ በየአካባቢው የሚያጋጥሙ ግጭቶች መነሻ የሆኑ መንስኤዎችን ለመፍታት ጉልህ ሚና እንዳለው አቶ አብርሃም ተናግረዋል።

በመሆኑም በየአካባቢው ህዝቡ ውስጥ ያሉ መልካም ኢትዮጵያዊ የሰላም ገንባታ እሴቶችን በማጠናከር ሀገራዊ ምክክሩ ግቡእንዲመታ ማድረግ ከኢትዮጵያዊያን እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

“በተለይም ሀገር የሁሉም መመኪያ ስለሆነች ባለፉት ጊዜያት በተሰሩ ሥራዎች የተፈጠረውን የፖለቲካ ስብራት ተነጋግሮ በመፍታት የጋራ ቤታችንን መያዝና መገንባት ይገባናል” ስሉም አስገንዝበዋል።

ሌላው የሀገር ሽማግሌ አቶ ገብረመድህን ቴቃ በበኩላቸው፣ በዎላይታ ባህል ማንኛውም በዳይና ተበዳይ የዎላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ “ጊፋታ” ከመምጣቱ በፊት እርቀ ሰላም እንደሚያወርድ ገልጸዋል።

በዚህ ጊዜ ከበዳይና ከተበዳይ ወገን አሸማጋዮች “ጉታራ” በሚሰኝ ስፍራ ተሰባስበው በችግሮቻቸው ላይ በግልፅ እንደሚነጋገሩም አስረድተዋል።

“አንቺም ተይ፤ አንተም ተው” በሚባባሉበት በእዚህ የእርቅ ማውረጃ ባህል በዳይና ተበዳይ ፍትሃዊ ዳኝነት እንደሚያገኙም ተናግረዋል።

“በነዚህ ባህላዊ የእርቀሰላም እሴቶች ይቅርታ የማያገኝ በደል የለም” ያሉት የሀገር ሽማግሌው፣ “ሀገራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታትና ሰላም ለማስፈን ከባህላዊ የሽምግልና እሴቶች ተሞክሮ ልንወስድ ይገባል” ሲሉም አስገንዝበዋል።

“ሀገራዊ ምክክሩ ቅራኔን ፈትቶ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ወሳኝ ሚና ስላለው እነዚህን ሰላም ማምጫ ባህላዊ እሴቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍ አድርጎ መጠቀም ይገባል” ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን በየማህበረሰቡ ያሉ ቱባ የግጭት መፍቻ ባህሎችን ዛሬ እንደሀገር ለገጠመን ችግር በመጠቀም አለመግባባቶችን በንግግር የመፍታት ባህል ሊያከበሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሀገር ሽማግሌዎቹ ባህላዊ የእርቅ አፈታት ሥርዓትን ለሀገራዊ ምክክሩ ለመጠቀም በሚደረግ ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ለኢዜአ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: