
የአሜሪካው ታይም መጽሔት በየዓመቱ የተጽእኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ማውጣት ከጀመረ ዘንድሮ 19ኛ ዓመቱን ይዟል።
መጽሔቱ ዛሬ ይፋ ባደረገው የ100 ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዝርዝር በአመራር ዘርፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መካተታቸውን አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እ.አ.አ በ2019 የመጽሔቱ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ አንዱ እንደነበሩ የሚታወስ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣የቻይናው ፕሬዝዳንት ዥ ጂንፒንግ፣የሩሲያው ፕሬዝዳንት ብላድሚር ፑቲን ፣ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ፣ የጀርመኑ መራኄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ፣ የታንዛንያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ሀሰንና የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን የአሜሪካው የዜና መጽሔት ታይምስ ዛሬ ይፋ ባደረገው የ100 ተጽእኖ ፈጣሪዎች ውስጥ ተካተዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይ ኤም ኤፍ) የቀድሞዋ ዋና ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ፣ የቶክ ሾው አዘጋጇ ኦፕራ ዊንፍሬይና የአፕል ዋና ስራ አስፈጻሚ ቲም ኩክ በዝርዝር ውሰጥ ከተካተቱ ግለሰቦች መካከል ይገኙበታል።
ታይስም መጽሔት የ100 ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ዝርዝር በዓለም ዙሪያ በመብቶች ተከራካሪነት፣በፈጠራና በስኬት የተዋጣላቸው የሚላቸውን ሰዎች ይሰይማል።
ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሆኑ ከሺህ በላይ የመጽሔቱ ተመራጮች ከመንግስት፣ንግድ፣ ከመዝናኛ፣ ከጤና፣ ከስፖርትና ከሳይንስ ዘርፎች የታዩ ናቸው።
ታይምስ የመጪው ትውልድ መሪዎች የሚላቸውንም በዚሁ የ100 ተጽዕኖ አሳዳሪዎች ዝርዝሩ ያካትታል።