ዛሬ አዳማ ላይ በተደረጉ የ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ማጠቃለያ ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ የደረጃ ዎላይታ ድቻ ደግሞ የፍፄሜ ጨዋታዎችን አሸንፈዋል።

ረፋድ 03:00 ላይ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም በተደረገው የደረጃ ጨዋታ የምድብ ሀ ሁለተኛው አርባምንጭ ከተማ እና የምድብ ለ ሁለተኛው ኢትዮጵያ ቡና ተገናኝተዋል። ጨዋታው የጥበቃ ኃይሎች እና የአምቡላንስ አገልግሎት በሌለበት መጀመሩ አግራሞትን የፈጠረ እና በቀጣይ ሊስተካከል የሚገባ ክስተት ሆኖ ተመልክተናል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ይዘው አርባምንጮች ደግሞ ከኳስ ውጪ ጠንቀቅ ብለው የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን በመፈለግ የጀመሩት ጨዋታ ጥሩ ፉክክርን ያስተናገደ ነበር። አደገኛ ሙከራዎች በብዛት ባይታዩነትም አርባምንጮች 24ኛው ደቂቃ ላይ የፊት አጥቂው ዮርዳኖስ እያሱ ከማዕዘን በተነሳ እና ቡናዎች በአግባብ ያላራቁትን ኳስ አግኝቶ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ ሆነዋል።

ከዚህ በኋላ የቡና የኳስ ንክኪዎች ለጎል ቀርበው ሲታዩ 30ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ጥቃት ሀቢብ ዛኪር ሳጥን ውስጥ ገብቶ የሞከረው ፣ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ በግራ የአጥቂዎቹ አማኑኤል አድማሱ እና ከድር ዓሊ አንድ ሁለት ቅብብል በከድር የተሞከረበት እንዲሁም 38ኛው ደቂቃ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ ወንድምአገኝ መላኩ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ሁለተኛው አጋማሽ በአመዛኙ የኢትዮጵያ ቡና የበላይነት የታየበት ነበር። ሆኖም ቡድኑ 54ኛው ደቂቃ ላይ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ቃለአብ ፍቅሩ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ውጪ እንደነበረው የኳስ ቁጥጥር በርካታ ዕድሎችን ሲፈጥር አልታየም። አርባምንጭ ከተማዎች አብዛኛውን ደቂቃ በጥንቃቄ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሲሆን ጨዋታው ወደ ፍፃሜው ሲቃረብ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በራሳቸው ሜዳ ላይ በመቅረት መሪነታቸውን አስጠብቀው ጨዋታውን በድል መወጣት ችለዋል።

ከሰዓት በኋላ ሁለቱን ምድቦች በበላይነት ባጠናቀቁት ዎላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ መካከል የተደረገውን ጨዋታ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዜዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ በክብር እንግድነት በመገኘት አስጀምረዋል። ጨዋታው በኢትዮጵያ ህዝብ ብሔራዊ መዝሙር የተጀመረ ሲሆን የዛሬ ዓመት ገደማ በድንገት ህይወቱ ላለፈው የቀድሞው የሀዋሳ ታዳጊ ግብ ጠባቂ አቤል አያኖ የህሊና ፀሎት ተደርጓል።

የዎላይታ ድቻ ከፍ ያለ የበላይነት የተንፀባረቀበት የመጀመሪያ አጋምሽ በጊዜ ግብ አስተናግዷል። 6ኛ ደቂቃ ላይ አማካዩ ሳሙኤል ደጊሶ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት ድንቅ የቅጣት ምት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከግቡም በኋላ ድቻዎች የጨዋታ ብልጫ ወስደው በቅብብሎች ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ታይተዋል። በሂደት ለመረጋት የሞከሩት ሀዋሳዎች 16ኛው ሰቂቃ ላይ ስጦታው ዓለማየሁ ከማዕዘን ምት በተነሳ ኳስ ካደረገው ሙከራ ውጪ ከባድ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ቀስ በቀስ የተጋጣሚያቸውን መነሳሳት ያቀዘቀዙት ድቻዎች 33ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ የቅጣት ምት መቺ መሆኑን ያሳየው ሳሙኤል ከቅጣት ምት በድጋሚ ሊያስቆጥር የተቃረበበትን ሙከራ አድርገዋል። ቡድኑ በግራ መስመር ይፈጥር በነበረው ጫናም በጥሩ ሂደት 39ኛው ደቂቃ ላይ ማስታዋል ገቻፎ ከመሀል ተቀብሎ ወደ ቀኝ በማጥበብ ያሳለፈለትን ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ዘላለም አባተ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ በመቆጣጠር ሁለተኛ ጎል አድርጎታል።

ሀዋሳ ከተማዎች ሁለተኛውን አጋማሽ በተነቃቃ መልኩ መጀመር ችለው ነበር። ተደጋጋሚ የቆመ ኳስ ዕድሎችን ያስገኘላቸውን ብልጫ ግን ወደ ውጤት ሳይቀይሩ ወላይታ ድቻዎች የቀደመ የጨዋታ የበላይነታቸውን መመለስ ችለዋል። ዘላለም በተሰለፈበት የቀኝ መስመር አድልተው የፈጠሩት ጫና ድቻዎች ጨዋታው በራሳቸው ቁጥጥር ስር እንዲዘልቅ ማድረግ ችለዋል። ቡድን 87ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በገባው ተመስገን ብርሀኑ ንፁህ የግብ ዕድል አግኝቶ ሳተ እንጂ ልዩነቱን ማስፋትም ይችል ነበር። ሆኖም የፍፃሜው ጨዋታ ሌላ ግብ ሳይቆጠርበት በወላይታ ድቻ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሁለቱ ግብ አስቆጣሪዎች ሳሙኤል ጃጊሶ እና ዘላለም አባተ
ከጨዋታው በኋላ በውድድሩ በጎ አስተዋፅዖ ያደረጉ የከተማ አስተዳደሮች እና ሌሎች አካላት እንዲሁም ተሳታፊ ክለቦች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል። በመቀጠል የዕለቱ የጨዋታ ዳኞች እንዲሁም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁት ሀዋሳ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ የሜዳሊያ ሽልማት ሲበረከትላቸው የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ፋሲል ከነማም ዋንጫውን ተረክቧል።

በመጨረሻም የውድድሩ አሸናፊ የሆነው ወላይታ ድቻ ቡድን አባላት የሜዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማታቸውን ተረክበው የሥነ ስርዓቱ ፍፃሜ ሆኗል ስል ሶኬር ኢትዮጵያ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *