ክቡር ዶ/ር መጋቢ ዮሐንስ ባሰና «በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ልማት አማካሪ ምክር ቤት» አባል በመሆን ለሠላማዊ መማር ማስተማር መረጋገጥ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የዕውቅና ሽልማት ተበረከተላቸው።

የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ከሰሞኑን የዩኒቨርሲቲው የሰላምና ልማት አማካሪ ምክር ቤት አባል በመሆን ለሠላማዊ መማር ማስተማር መረጋገጥና መዝለቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላባረከቱት ክቡር ዶ/ር መጋቢ ዮሐንስ ባሰና የእውቅና ሽልማት አበርክቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የፕሬዝዳንቱ ተወካይ ዶ/ር አብርሃም ቦሻ፤ ክቡር ዶ/ር መጋቢ ዮሐንስ ባሰና በዩኒቨርሲቲው የሠላምና ልማት አማካሪ ምክር ቤት አባል በመሆን ለሠላምዊ መማር ማስተማር መስፈንና መጎልበት ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ተቋሙ ከፍተኛ ምስጋና እንዳለው ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር፣ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ሌሎች ልማታዊ ሥራዎች ስኬታማነት የክቡር ዶ/ር መጋቢ ዮሐንስ ባሰና የላቀ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው የፕሬዝዳንቱ ተወካይ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው ከሌሎች የአማካሪ ም/ቤት አባላት ጋር በመሆን የተሰጣቸውን ሐላፊነት በቅንነት እየተወጡ መቆየታቸውን ዶ/ር አብርሃም ጠቁመው፤ ሌሎችም እንደ ክቡር ዶ/ር መጋቢ ዮሐንስ ባሰና ስለሀገርና ስለአካባቢ ፍቅር ገብቷቸው ለሰላም፥ ለልማት በአጠቃላይም ለመልካም ሥራ እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል።

መርሃ ግብሩን የተገኙት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው፤ ክቡር ዶ/ር መጋቢ ዮሐንስ ባሰና በመልካም ስነ-ምግባር የታነጹ ዜጎች በማፍራት እንዲሁም ለሰላምና ለልማት መረጋገጥ የነበራቸው አበርክቶት ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

ክቡር ዶ/ር መጋቢ ዮሐንስ ባሰና በዎላይታ ዞን ሰላም እንዲሰፍንና ልማት እንዲረጋገጥ በበጎ መልኩ ሲንቀሳቀሱ የሚታዩ ቅን አባት መሆናቸውን አቶ አክሊሉ ጠቁመው፤ በቀጣይ ጊዜያት በመልካም ስብዕና ግንባታ ላይ የነበራቸው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ክቡር ዶ/ር መጋቢ ዮሐንስ ባሰና የሰውን ልጅ ያለ አንዳች ልዩነት የሚያዩ ታላቅ ቅን ሰው መሆናቸው በህይወት ምስክርነት ተገልጿል።

ክቡር ዶ/ር መጋቢ ዮሐንስ ባሰና ለዎላይታና አካባቢው ሆነ ለመላው ኢትዮጵያ የምክር፣ የሰላም እንዲሁም የእርቅ አባት መሆናቸው በመድረኩ የተጠቀሰ ሲሆን፤ በህይወታቸው ለአካባቢው ማህበረሰብ ምሳሌ በመሆን የኖሩና እየኖሩ ያሉ ታላቅ የእምነት አባት ስለመሆናቸው ተጠቅሷል።

ክቡር ዶ/ር መጋቢ ዮሐንስ ባሰና በህይወታቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን በመድረኩ የገለፁ ሲሆን፤ በሁሉም አካባቢ የሚኖሩ መላው የሰው ልጆች ለፈጣሪ፣ ለአካባቢው ሰው እንዲሁም ለመንግስት ታማኝ በመሆን መንቀሰስ ተገቢ እንደሆነ ምክር ለግሰዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ለክቡር ዶ/ር መጋቢ ዮሐንስ ባሰና የአንገት ሀብል ወርቅ፣ የእጅ ቀለበት ወርቅ፣ የገንዘብ እና የዋንጫ ሽልማት ተበረከቶላቸዋል።

የዩንቨረስቲው ኮሙኒኬሽን የላከልን መረጃ እንደሚያመለክተው መርሃ ግብሩን ዩኒቨርሲቲው ከዎላይታ ሽማግሌዎች ጉባኤ (ጉተራ) ጋር በትብብር ያዘጋጁት መሆኑን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አሳውቋል።

የተከበሩ ዶ/ር መጋቢ ዩሐንስ ባሰና በቅርቡ በወንጌል አገልግሎት ዘርፍ የክብር ዶክትሬት ድግሪ ከገሊላ ኢንተርናሽናል ሴሚናሪ መቀበላቸው ይታወቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *