1653667989019

በደቡብ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ችግሮችን ከስሩ ለማስወገድ የችግሮችን መነሻ ምክንያት በመለየት እንዲፈቱ እቅድ መያዙ ተገለፀ፡፡

የደቡብ ክልል የፀጥታው ምክር በወቅታዊ ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው ዕለት በዎላይታ ሶዶ ከተማ ያካሄደውን አስቸኳይ ውይይት በቀጣይ 1 ወር ውስጥ የሚደረጉ ተግባራትን በመወሰን ተጠናቋል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ መግለጫ የሰጡት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ በክልሉ አብዛኛው አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶች ከአደረጃጀትና ከመዋቅር ጥያቄ ከአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳይ እንዲሁም ከኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች የተነሳ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህን ችግሮች በመጠቀም ህዝብን ለግጭት የሚያነሳሱ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከአደረጃጀትና ከመዋቅር ጥያቄ ጋር በተያያዘ ሚነሳ ጥያቄ በህገ መንግስቱና መሰረት የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጦላቸው ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት ለመፍታት ውሳኔ ተላልፏል ብለዋል፡፡

ከአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳይ እንዲሁ ለግጭት መንስኤ እንዳይሆኑ በአሰራር እና ደንብ መሰረት መንግስትና ህዝብ በጋራ በመሆን በውይይት እንዲፈታ ውሳኔ መተላፉን ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል እነዚህን ግጭቶች በባለቤትነት የተሳተፉና የደገፉ የመንግስት አመራሮች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ከማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሀሰተኛ ገፅ በመክፈት ህዝብን ከህዝብ ሲያጋጩ የቆዩ አካላትን በማጣራት በሀሰተኛ መረጃቸው ምክንያት ለደረሰ ጉዳትና ኪሳራ ሁሉ እንዲጠየቁ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

ችግሮችን በመነጋገር ከመፍታት ይልቅ ታጥቀው ጫካ በመግባት የህዝብን ሰላም የሚያደፈርሱ ቡድኖችንም ከህዝቡ ነጥሎ በተጠናከረ መልኩ ሕግ የማስከበር ስራ እንዲሁም የግንዛቤ ስራ ተሰርቶ እጅ የሚሰጡ ካሉ እርምት እንዲወሰድ ለማድረግም የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገልፀዋል ሲል ዎቴቪ ዘግቧል።