“በማህበራዊ ትስስር ገጾች በሚሰራጭ ሀሰተኛ መረጃ የሚፍረከረክ አፍራሽ አስተሳሰብ ያለውን ትውልድ ሳይሆን ዕውቀትና ክህሎት ያለው፥ በስነ-አመክንዬ የሚያምን ትውልድን ለማነጽ በትጋት እንሰራለ።”- ፕ/ር ታከለ ታደሰ

የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የ2014 ዓ.ም ምሩቃን እና የ1ኛ ዓመት ተማሪዎች ጋር በ4ኛ ዙር አረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም ትግበራ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል።

«ዐሻራችን ለትውልዳችን» በሚል መሪ ቃል ለሚደረገው የ2014 ዓ.ም 4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዩኒቨርሲቲው 550 ሺህ ችግኞችን በማፍላት የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ አጠናቋል።

ዩኒቨርሲቲው ሐምሌ 1/2014 ዓ.ም በዓይነቱ ለየት ያለ እና በአንድ ጀምበር 10 ሺህ ችግኝ የሚተከልበትን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ እና ከዎላይታ ዞን ግብርና መምሪያ ጋር በመተባበር አዘጋጅቷል።

በመርሃ ግብሩ የፌዴራል፣ የክልል፣ የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ በደቡብ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶች፣ የሠላምና ልማት አማካሪ ምክር ቤት አባላት፣ የካውንስል አባላት፣ የተቋሙ ሠራተኞች፣ የ2014 ዓ.ም ዕጩ ምሩቃን እና የ1ኛ ዓመት ተማሪዎች እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል።

በዚሁ በመርሃ ግብር ለሚሳተፉና ከ6 ሺህ ለሚበልጡ ለዩኒቨርሲቲው የ2014 ዓ.ም ምሩቃን እና ለ1ኛ ዓመት ተማሪዎች በፕሮግራሙ ትግበራ ላይ ያተኮረ ገለጻ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ እንደ ተቋም በቅርቡ የሚመረቁ ተማሪዎች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ ለስኬት መድረሳቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ተወዳዳሪ፣ ብቁ እውቀትና ክዕሎት ያለው ምሩቅ ለማፍራት በትምህርት ልማት መስክ በተቀናጀ መልኩ እየሰራ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ እጅግ ተወዳዳሪ ለማድርግ ብሎም ብቁ ምሩቃን ተማሪዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማፍራት  አበክረን እየሰራን ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ አበክሮ የሚሰራ፥ገለልተኛና ሁሉንም በእኩል የሚያስተናግድ ሕብረ-ብሔራዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በመገንባት፥ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ወንድማማችነት የሰፈነበት ተቋም መገንባት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ነውፕ/ር ታከለ ያሳወቁት።

ከብልሹ አሰራር የጸዳ፣ ከስነ-ምግባር ጥሰት የተላቀቀ እጅግ ተወዳዳሪ እና ብቁ ትውልድ ማፍራቱ እንደ ተቋም ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አሳውቀዋል።

ሠላማችንን ለማስከበር እጅ ለእጅ ተያይዘንና ተቀናጅተን መስራት አለብን ያሉት ፕ/ር ታከለ፤ ዩኒቨርሲቲው ለሰላም ጉዳይ የቅድምያ ቅድምያ ይሰጣል ሲሉም ጠቁመዋል።

ሠላም ሁለንተናዊ ተነሳሽነትን ይጠይቃል፥ ሠላም መሰጠትን ይጠይቃል፥ ሠላም አብሮ መስራትን ይጠይቃል ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ አዲስ ገቢ ተማሪዎች የነባሮችን ልምድ በመቅሰም በተቋም ቆይታቸው «የሰላም አምባሳደር» በመሆን ከአጀንዳ ተሸካሚነት ተላቀው ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ አሳስበዋል።

በማህበራዊ ትስስር ገጾች በሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች የሚፍረከረክ እና አፍራሽ አስተሳሰብ ያለውን ትውልድ ሳይሆን ዕውቀትና ክዕሎት ያለውን ብሎም በስነ-አመክንዮ የሚያምን ትውልድን ለማፍራት በትጋት እንሰራለን ሲሉም ፕ/ር ታከለ ተናግረዋል።

“በመንጋ በማሰብ እና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን በመንጋ በመተግበር” ለውጥ ፈጽሞ ሊመጣ አይችልም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፤ “ዕውቀትን በተግባር በመግለጽ” በሀገሪቱ አዎንታዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት በዕውቀት መመራት ግድ ይላል ብለዋል።

“ለውጥ በቆሞ ቀር አስተሳሰብ አይመጣም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “ተራማጅ ዘመናዊ አስትሳሰቦችን በእውቀት በመተግበር ተቋማዊ እና ሀገራዊ የልማት እምርታ እንዲመጣ ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር በአጋርነት እና ትብብር መስክ የጀመርናቸውን ተግባራት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ተቋማዊ አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በማድረግ «ዲጂታል ዩኒቨርሲቲ» ለመገንባት በስፋት እየተሰራ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ዩኒቨርሲቲውን ለማዘመን የሚደረገው ጥረት በተቀናጀ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲ በ2022 ዓ.ም “ቴክኖሎጂ መር የግብርና እና ጤና ልዕቀት ማዕከል” ለመሆን እየሰራ ነው ያሉት ፕ/ር ታከለ ፤ በ2015 ዓ.ም «22 ሚሊየን» የሚገመት የአትክልትና የፍራፍሬ ምርት በዩኒቨርሲቲው በሚገኝ የእርሻ ስፍራ በማምረት ሀብት ለማትረፍ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነም አሳውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለ4ኛው ዙር የ2014 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም የሚውል 550 ሺህ የደን እና ለምግብነት የሚያገልግሉ የፍራፍሬ ችግኞችን ለተከላ ማዘጋጀቱን ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲው በሚደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የ2014 ዓ.ም ተመራቂዎች ሐምሌ 01 እና 08/ 2014 ዓ.ም ችግኝ እንዲተክሉ ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ሁሉም የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች እስከ ሐምሌ 30/2014 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት እያንዳንዳቸው 100 ችግኝ እንዲተክሉ ፕ/ር ታከለ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ፕሬዝዳንቱ፤ የትምህርትና የምርምር ጥራትና ተገቢነትን ማረጋገጥ፣ የመሠረተ-ልማት እና የግንባታ ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ማሻሻል፣ የሃብት አስተዳደርና ተጠያቂነት ማስፈን፣ ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ መስጠት፣ ሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደት ማረጋገጥና ማዝለቅ በቀጣይ እንደ ተቋም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን አመላክተዋል ስል የዩንቨርስቲው ኮሙኒኬሽን ዳይሮክተሬት ያደረሰን ዘገባ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: