Photo_1657206363184

በክልሉ የማንነት፣ የወሰንና የአደረጃጀት ጥያቄዎች መነሻ በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ሰዎች ለተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት እየሆነ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን ገልጿል።

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት ነፃነታቸውን በሕገ ወጥ እና በዘፈቀደ የተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ያተኮረ የመጀመሪያ ብሔራዊ ህዝባዊ ምርመራ ሂደት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን በዛሬው ዕለት በሐዋሳ ከተማ ለተለያዩ ሚዲያዎች ሰጥቷል።

መግለጫውን በጋራ ከሰጡት መካከል የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ እንደገለፁት ብሔራዊ ምርመራ ግልጽ እና በሕዝባዊ ተሳትፎ መንገድ የሚደረግ እና የመብቶች ጥሰት የደረሰባቸው ተጎጂዎች፣ ምስክሮች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በአንድ መድረክ በተገኙበት የሚከናወን የምርመራ ስልት በመሆኑ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዝ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይም በደቡብ ክልል የማንነት፣ የአስተዳዳርና የአደረጃጀት ወሰን የአደረጃጀት ጥያቄዎች ምንክያት የሚከሰቱ አለመግባባት ሰዎችን ያለፍርድቤት ትዕዛዝ ህገወጥ መታሰር፣ ጭካኔ የተሞላበት አያያዝ፣ የፓለትካ ልዩነትን መሠረት ያደረገ እስር፣ ፍርድቤት በቀጠሮ ማመላለስና ለተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት እየሆነ መሆኑን በምርመራ ሂደት ተነስቶ በመፍትሔ አቅጣጫ መወያየታቸውን ኮምሽነር ራከብ አብራርተዋል።

የመጀመሪያ ብሔራዊ ህዝባዊ ምርመራ ሂደት በሀገር አቀፍ ደረጃ ወይም በበርካታ አካባቢዎች የሚታዩ ውስብስብና ተደጋጋሚ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ቀልጣፋ እና ተደራሽ በሆነ መልኩ ለመመርመር እና ሥርዓታዊ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ የሚጠቅም ዘዴ መሆኑንና ምክትል ዋና ኮምሽነር አክለው ተናግረዋል።

የኢሰመኮ የሴቶችና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫውን በጋራ ሲሰጡ በተለይም በደቡብ ክልል የማንነት፣ የወሰን እንዲሁም የአደረጃጀት ጥያቄዎችን መነሻ ተደርጎ በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ሰዎችን ያለፍርድቤት ትዕዛዝ ህገወጥ መታሰር፣ ጭካኔ የተሞላበት አያያዝ፣ የፓለትካ ልዩነትን መሠረት ያደረገ እስር፣ በቀጠሮ ረጅም ጊዜ ፍርድቤት ማመላለስና ለተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዋናነትና በተደጋጋሚ ከሚከሰትባቸው ቦታዎች ጋሞ ዞን፣ ዎላይታ ዞን፣ ኮንሶ ዞን፣ ደራሼ እንዲሁም በጉራጌ ዞን መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከማኅበረሰቡ የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን እውቀት እና ልምድ፣ በተያዘው ጉዳይ ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች
ሲያከናውኑት በነበረው ሥራ እንዲሁም ምሁራን ባደረጓቸው ጥናቶች እና ምርምሮች ላይ መሰረት ያደረጉ የሕግ ክፍተቶች እና የአሰራር ጉድለቶችን በምርመራ መድረኩ ላይ መነሳቱን በመግለጫቸው የገለፁት ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በቀጣይ የፍትሕ እና የወንጀል አስተዳደር አካላትን ጨምሮ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተጎጂዎች ባነሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ምላሽ እና የመፍትሔ ሃሳቦቻቸውን መግለፃቸውን የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ጨምሮ ሌሎች ሚዲያዎች በተገኙበት ተናግረዋል።