1649043617346

ስፖርት ለህዝብ ከሚያስገኝለት የጤና እና በመልካም ስብዕና የተገነባ ማህበረሰብ (ወጣት) ከመፍጠር ባለፈ በዘመናችን የሀገር ኢኮኖሚ መሰረት እስከመሆን እንደደረሰ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው።

በሀገራችንም በአትሌቲክስ ዘርፍ ሀገርንና ህዝብን ከመወከል አንስቶ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የጨመረው አበርክቶ ቀላል አይደለም። እንደ ሀገር ብዙ ባንጠቀምበትም በግለሰብ ደረጃ ግን ፍሬዎች አሉ። ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ አትሌቶችን ስም መዘርዘሩ ለቀባሪ የማርዳት ያህል ይሆንብኛል።

በርግጥ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእግርኳስ ዘርፉም ቢሆን እንደ አፍቃሪው ብዛት ወደ ኢኮኖሚ ቀይረነው ባንጠቀምም ዳዴ ማለቱን ስንመለከት ተስፋ ሰጪ መሆኑን እንገነዘባለን።

ከላይ በመግቢያዬ ለመግለፅ እንደሞከርኩት የስፖርት ዘርፍን ከጤና እና መዝናኛነቱ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን ብናውቅም የዎላይታ ዞን መንግስት በስፖርት ዘርፍ በዋናነት በእግርኳስ ላይ ከዎላይታ ዲቻ ጋር በተያያዘ ምን መስራት አለበት የሚለውን እንደምሳሌ የምንመለከት ይሆናል።

በርግጥ በዎላይታ ውስጥ በተጨባጭ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ብዙ የስፖርት ዘርፎች አሉ። በዋናነትም የቮሊቦል፣ የአጭር ርቀት ሩጫ፣ የቦክስ፣ የብስክሌት እና የእግርኳስ  ውድድሮች ዋነኞቹ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ የእግርኳስ ዘርፍ ብዙ ችግሮች ቢኖሩበትም በተሻለ መልኩ በአካባቢው ላይ ውጤታማ ለማድረግ እየተሞከረ ይገኛል።

በአንፃራዊነትም የዎላይታ ዲቻ ስፖርት ክለብ በተሻለ ደረጃ ላይ ቢገኝም ክለቡ ለሌሎች የአከባቢው የስፖርት ዘርፎች እንደ ምሳሌ ተጠቅሶ እንደ ክለብ መሻሻል የሚገባቸውን ነጥቦች በስድስት በመክፈል እንደሚከተለው እንመለከታለን።

በመጀመሪያ አስተዳደር ወይም አደረጃጀትን ብንመለከት መልካም ነው። ምክንያቱም የአንድ ክለብ ውጤትም ሆነ ውድቀት የሚመጣው ክለቡ በሚመራበት መንገድ ነው። ለዚህ ደግሞ የክለብ ማኔጀር(አስተዳደር) የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።

በእኛ ሀገር አብዛኛው የእግርኳስ ክለብ በመንግሥት በጀት የሚንቀሳቀስ ከመሆኑ አንፃር የመንግስት አካላት የሚዘውሩት እንደሆነ ግልፅ ነው። ዘርፉ ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ ነው። በክለቡ ውስጥ ያለ ማንኛውም አካል ቢሰራም ባይሰራም ይከፈለዋል። ከክለቡ ጋር ድሬዳዋ ነኝ እያለ ዎላይታ ሶዶ ቁጭ ብሎ አበል ይቀበላል ማለት ነው። ይህ ደግሞ የውድድር ስሜትን በእጅጉ ይጎዳዋል። የዎላይታ ዲቻ ስፖርት ክለብም የዚህ ገፈጥ ቀማሽ ክለብ ነው። ቢያንስ ክለቡ በረጅም ጊዜ ወደ ግል ከመዛወሩ በፊት መች ከመንግስት ትከሻ ወርዶ እንደሌሎች ገቢ አምጪ ጅርጅቶች እንደሚቋቋም አይታወቅም። 

ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ አላማ ወይም ግብ አለማስቀመጥ ነው። አላማ የሌለን ቡድን መደገፍ በራሱ አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ ክለቡ በ2014ዓ.ም በፕሪሚየር ሊጉ እንዲቆይ ከመነገሩ ውጪ ስንተኛ ሆኖ መጨረስ እንዳለበት የተቀመጠ ምንም አይነት የአመቱ ግብ የለም። አንደኛ? አስረኛ? ወይስ አምስተኛ? ምንም አይታወቅም።

ስለዚህ በየአመቱ ደረጃው ግልፅ ሆኖ መቀመጥ አለበት። በፕሪሚየር ሊግ ውስጥ እንዲቆይ የሚለው በራሱ ግልፅ አይደለም። ለምሳሌ በ2015 ዓ.ም በሦስተኝነት፣ በ2016 ዓ.ም ሁለተኝነት እና የኮንፌዴሬሽን ተሳታፊ  መሆን። በኮንፌዴሬሽኑም ወደ ምድብ ድልድል ውስጥ መግባት…ወዘተ የሚሉ ግልፅ ግቦች በሀገርም ሆነ በአፍሪካ እንዲሁም በአለም ደረጃ ተሳትፎን ታሳቢ ተደርጎ  ሊቀመጥ ይገባል። ክለቡ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅዱን አስቀምጦ ለደጋፊው ግልፅ ማድረግ አለበት።

ከዚህ ጋር በሚመጋገብ መልኩ የተጫዋቾች አያያዝ ተገቢውን ቁጥጥር ይፈልጋል። ተጫዋቾች ፕሮፌሽናል ኤቲክስ እንዲጠብቁ ክትትል ከማድረግ በተጨማሪ አዲስ የሚፈርሙትን ሆነ ከታች የሚያድጉትን ክለቡ በአመቱ ለታሰበለት አላማ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ለምሳሌ አምና ከክለቡ ከአራት በላይ ወሳኝ ተጫዋቾች በአንዴ ሲለቁ የክለብ አስተዳደር ምንም ማድረግ አለመቻሉ ክለቡ አላማ ቢስ እንደሆነ ያሳያል።

በዚያው ልክ አመቱን በሙሉ አንድ ጨዋታ እንኳ ሳይጫወቱ የተቀመጡ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች እንዳሉ ይታወቃል። ምን ይሰራሉ? በተጨማሪም ክለቡን የለቀቁ ተጫዋቾች ከታች ክለቡ ኮትኩቶ ያሳደጋቸው ከመሆኑ አንፃር በነፃ ለቋቸው ሲታይ በኮንትራት ውስጥም ክለቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚጠበቅበት ያመላክታል። ስንት ዘመን አሰልጥኖ በነፃ መልቀቅ በራሱ ለክለቡ ኪሳራ ነው። ይታሰብበት!

ሦስተኛው ውጤትን የሚመለከት ነው። ዲቻ ብራንዱ ከፍ ማለት ካለበት ውጤት የክለቡ የጀርባ አጥንት ነው። ያለውጤት ክለቡን በራሱ እንዲቆም ለማድረግ ማሰብ እብደት ነው። ክለቡ አሁን ካለበት እጅግ በጣም ከተቀዛቀዘ አጨዋወት መውጣት አለበት።

እውነት ለመናገር ለአቻ ውጤት መጫወትን ሊያቆም ይገባል። ይህም የውጤት ባህሪ ከክለቡ አላማ የለሽነት ጋር እጅግ በጣም ይቆራኛል። ክለቡ ውጤት ሲያጣ አሰልጣኙ “ዘንድሮ ከክለቡ አመራሮች ጋር የተነጋገርኩት ክለቡን በሊጉ ለማቆየት ብቻ ነው” ይላል።

ምንም ጥፋት የለበትም። በነገራችን ላይ ክለቡ እቅድ ካለው አሁን ያለውን አሰልጣኝ እና ተጫዋቾች በማቆየት ከታች የሚያድጉትንም በመጨመር ስራውን መጀመር አለበት። አላማ  ከውጤት ጋር ሲዋሀድ የገቢ ምንጭ ይሆናል።

ለዎላይታ ወጣት የገቢ ምንጭ ሊሆን የሚገባው የግድ በኮብልስቶን ሥራ ማደራጀት እና ሼድ ማደል ብቻ አይደለም! አመራሩ በአከባቢው የሚገኙ ግብአቶች(resource) በሚገባ ተጠቅሞ ሀብት ማፍራት አለበት። ከዚህ ውስጥ አንዱ ስፖርት ነው!

አራተኛው የማለያ እና ሌሎች ነገሮች ሽያጭ ሲሆን ከውጤት ጋር እጅግ በጣም የተቆራኘ ነው። ውጤት ሲኖር ደጋፊ ስቴዲየም ይሞላል። ማለያ ይቸበቸባል። ውጤት ከሌለ ወፍ የለም! ስለዚህ ውጤትን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው የገበያ አጋጣሚ ቀላል አይደለም። ይህን በደንብ መጠቀም ላይ ክለቡ ከፍተኛ ችግር አለበት።

በዘንድሮ የዲቻ ውጤት ደህና የነበረው በመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ነበር፤ ማለያው የደረሰው ግን በሁለተኛው ዙር ማለቂያ አከባቢ ነው። አራምባና ቆቦ ማለት ይህ ነው። በዛ ላይ የማለያው ዲዛይን እንኳን ሊገዛ ቀርቶ ለከፍተኛ ትችት ያጋለጠ ነበር። በነገራችን ላይ አንድ ክለብ በማለያ ሽያጭ ብቻ ገቢ ያግኝ ያለው ማነው? ስንት ነገር በዲቻ ከለር ተሰርቶ መሸጥ እየተቻለ? በዚህ ጉዳይ ከክለቡ አመራሮች በተሻለ የዲቻ ቡና እና ቁርስ ቤት ባለቤት የገባት ይመስለኛል። ደሞ ሄዳቹ አፍርሱ አሉ። እግረመንገዴን ዲቻ ሁዋላ ቀር ሎጎውን እንዲቀይር እጠይቃለሁ።

ሌላው ወሳኝ ነገር የክለብ ሚዲያ ነው። ዲቻ የህዝብ እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱ አሰራር እና ሂደት በግልፅ በራሱ በክለቡ ሚዲያ በሚስብ አቀራረብ ጊዜውን በጠበቀ መልኩ መገለፅ አለበት። በሚዲያው አለም ጊዜ(timing) እጅግ በጣም ወሳኝ ነው። ይህንን በዲቻ ቤት ፈፅሞ አንመለከትም። የክለቡ ድህረገጽ አለ ይባላል ነገር ግን ከፍቶ ለማየት አስቸጋሪ ነው። ምንም አይነት የተደራጀ ሚዲያ የለውም። ቢኖረውም ከሶከርኢትዮጵያ ኮፒ ፔስት አድርጎ ከማቅረብ የዘለለ ስራ የለውም። ቢታወቅበት ግን የክለቡን ድህረገጽ በማስታወቂያ ማጥለቅለቅ ይቻል ነበር። ለክለቡም እንደ አንድ የመረጃ ማቃበያ ከመሆኑም ባሻገር የገቢ ምንጭ ይሆን ነበር። እረ ለመሆኑ የክለቡን ዋና እና ታዳጊ ልጆችን ቪዲዮ ሰርቶ በድህረገጹ ላይ በማጋራት ከታዳጊ ተጫዋቾች የስንቱን እንጀራ አብስሎ ክለቡ ደግሞ ለራሱም ከሽያጬ ገቢ ያገኝ ነበር?

ከላይ የገልፅናቸው ነገሮች ካሳካን የስፖንሰርሺፕ ጉዳይ ቀላል ይሆናል። ማንም ሰው ሆነ ድርጅት ከአሸናፊዎች ጋር መጓዝ ይወዳል። አሸናፊ ከሆንክ ቢወድህም ባይወድህም ስሙን ከአንተ ጋር ለማጣመር ወደ አንተ ይመጣል። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ዲቻ ስፖንሰር መፈለግ ግዴታው ነው። ቢያንስ የክለቡን የማለያ ወጪ የሚሸፍንለትን ድርጅት ማፈላለግ ግዴታው መሆን አለበት። እኔ በበኩሌ የንብ ባንክን እንድታናግሩ እመክራለው ሌላው ቢቀር እኛ የጦና ንቦች ነን።

በመጨረሻም ማለት የምፈልገው የዚህ ፅሁፍ መነሻዬም ሆነ መድረሻዬ ዎላይታ ዲቻ ስፖርት ክለብ አድጎ ለማየት፤ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካና በአለም ተወዳድሮ ውጤትና ገንዘብ ይዞ እንዲመጣ ካለኝ ከፍተኛ እና ፅኑ ፍላጎት የተነሳ ብቻ እንደሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። ሌሎችም ክለቦች ማለትም የቮሊቦል ክለቦችም በውጪ ከመሳተፍ በተሻገረ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ከማሰብ፤ እነ ሶዶ እና ቦዲቲ ከተማም በዚህ ልክ እራሳቸውን ከወዲሁ እንዲያደራጁ ካለኝ ፍላጎት ነው። ለሀገር ምሳሌ መሆን በዎላይታ አሁንም ይቀጥል! አመሰግናለሁ።

ሀብቴ በዛብህ ፎላ