1658131610146

ዳውሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሙስና ወንጀል በተከሰሱ ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላለፈ።

የዳውሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሙስና ወንጀል በተከሰሱ 3 ግለሰቦች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል።

ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ የኢፌዴሪ ሙስና ወንጀል አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32/4/ እና 23/2/ እንዲሁም አንቀፅ 9/2/ በመተላለፍ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘትና   የሌላ ሰው ጥቅም ወይም መብት ለመጉዳት አስበው በፈፀሙት የሙስና ወንጀል መሆኑን አብራርቷል።

ተከሳሾቹ የደቡብ ብ/ብ/ህ/ክልል ጤና ቢሮ ደብዳቤ እንደፃፈ በማስመሰል የሀሰት ደብዳቤ በማዘጋጀት በቀን 06/20/2014 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ሰዓት አከባቢ በቃራዎ ጤና ጥበቃ ፅ/ቤት ውስጥ የነበረውን ግምቱ ከ4 ሚልዮን ብር በላይ የሆነ የፀረ ተባይ ኬሚካል የታርጋ ቁጥሩ 91437 በሆነው ስኖትራክ መኪና ጭነው ልወጡ ሲሉ ከአከባቢው ህብረተሰብ በደረሰው ጥቆማ መሠረት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የችሎት መዝገቡ አመላክቷል ።

የክስ መዝገቡን ስመረምር የቆየው የዳውሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 30/2014 በዋለው ችሎት:-

1ኛ ተከሳሽ በሆኑ በአቶ ባህሩ ቀልታ እጅ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በሚታሰብ የ3 ዓመት ፅኑ እስራትና 3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ

2ኛ ተከሳሽ በሆኑ በአቶ ታረቀኝ ድናቶ በሁለት አንቀጾች እጅ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በሚታሰብ የ4 አመት ፅኑ እስራትና 5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ

3ኛ ተከሳሽ በሆኑት በአቶ መብራቱ ማቲዎስ በሁለት አንቀጾች እጅ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በሚታሰብ የ4 አመት ፅኑ እስራትና 5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል ።

ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ጥቆማ በመስጠት የተባበሩትን ያመሰገነው የዳውሮ ዞን ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግኑኝነትና ግንባታ ዲቪዥን የመንግስትና የህዝብ ስልጣንን ተጠቅሞ ያለ አግባብ ለመበልፀግ የሚፈልጉ አካላት ከመሰል ድርጊት እንዲቆጠቡና ማህበረሰቡም ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የተለመደውን የወንጀል መከላከል ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል ።

ዘገባው: የዳውሮ ዞን የመን/ኮ/ጉ/ መምሪያ ነው።