ላላሺሞ!! ጊዲ ናኢዮ ኤኪዲ ይዳ_ዎላይታ-ኢትዮጵያ 🤲

ባህሉን አክባሪ ትውልድ ይለምልም!!

ከሊሞዝን ሽርሽር፣ ከመናፈሻ ኬክ ቆረሳ መዝናኛ፣ ከመኪና ጡሩምባና ጋጋታ፣ ከአዳራሽና ከድንኳን ኪራይ ወዘተ ጣጣ ይልቅ የሕዝባችንን ባህላዊ ጋብቻ ሥነ ሥርዓት Restoration ለማስጀመር በማሰብ ትልቅ ጅማሮ አድርገዋልና ባህላቸውን አክባሪ ለማንነታቸው ተቆርቋሪ ጀግኖቻችን ወንድሜ መሣይ ጳውሎስና እህቴ እየሩሳሌም መርዕድ የዎላይታን ሕዝብ ባህላዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓትን ለመታደም ወርቃማ ዕድል ስለ ፈጠራችሁልን አመሰግናለሁ፤ ዘራችሁ ይባረክ፤ ዉለዱ ክበዱ፡፡ የጉዞ ማስታወሻ ~ ~ ~ ~

በ10/11/2014 ዓ/ም ከጧቱ 3:00 አከባቢ ከዳሞታ ፀዳል ዎላይታ ሶዶ ከተማ ከተለመደው የሠርግ መኪኖች በተቃራኒው ጠንካራ፣ከፍታና ጉልበት ያላቸውን መኪኖች አሰልፈን በማረሚያ ቤት ቁልቁለት ተጉዘን ወደ ቀኝ ታጠፍንና የክቡር አባታችን አባባ ዋና ዋጌሾን 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በስተግራ አባ ፓስካል የልጃገረዶች ት/ቤት ግቢ በስተ ቀኝ አቋርጠን ኢትቡሩክ የሚባል ድርጅት ከ45 ዓመታት በፊት በተሰራው ገና ወደ አስፋልት ደረጃ እያደገ በሚገኘው ሶዶ ሣውላ- ጎፋ- -ጂንካ መሥመር ይዘን መዳረሻችን ወደ ሆነው ወደ ጀግኖች ምድር “ካዎ ኮይሻ ቦሎላ ጉታራ” ጉዞ ቀጠልን፡፡

ቶሜ ጌሬራ በተንጣለለው ሜዳ ቆመን ወደ ኬንያ የሚሄደውን ባለ 500 Volt የኤሌክትሪክ መሥመር ስናይ ቦታው ሰፋፊ ኢንዱስትሪዎችን ለመሸከም የሚመኘውን እየቃኘን በዕለቱ የነበረው ቅዝቃዜና ጉም የጉዟችንን መዳረሻ ከርቀት እንዳናይ ከልክሎናል በሾፌራችን የሙዚቃ ምርጫ እየተዝናናን ቀልጠፍ ባለ ጉዞ ወደ ፊት ቀጠልን፡፡

የባጋጀ አይዛን (ያዮራ ጎዳ) ዋጪጋ ቀበሌ አልፈን በካሳቫ (ሚታ ቦዬ) ማሣ እየተማረክን ከሶዶ 29 ኪ/ሜ ተጉዘን የአዴቶ ናዶ ኦፋ ወረዳ ዋና ከተማ ገሱባ ደረስን፡፡

ጉዟችንን ወደ ቀኝ አቅጣጫ በመቀጠል የሀገር ወዳዱን የሕዝብ ልጅ ሟች አባታችን አየለ አዳሬን ማሣ አቋርጦ የሚሄደውንና የደሜ ወንዝ ገባር የሆነውን ትልቁን የማንኢሣ ወንዝ ተሻግረን ኦቻ (ዶቅማ)፣ ጋሣ እና መሠል ወንዝ ዳር የሚበቅሉ እንጨቶችን እየቃኘን የአቀበት ጉዞ ጀመርን፡፡

የአርቲስት አለማየሁ ዛሳን የትውልድ መንደር ዳቃያ አልፈን ጥንታዊቷን የባይራ ኮይሻ ወረዳ በቅሎ ሰኞ ከተማን ወደ ቀኝ በመተው ጉዟችንን ወደ ፊት ቀጠልን፡

በ1990ዎቹ መጨረሻ 10ኪ/ሜ ኮንክሪት አስፋልት ሶዶ ከተማ ሲሰራ የመንገዱን የምህንድስና ሥራ ሙሉ በሙሉ በነፃ የሰራውንና የአ/አ አብይ ኮሚቴ አባል የነበረው የኢንጅነር ያዕቆብ ጋባቶ ትውልድ መንደር ሣዶዬ ቀበሌ እንደደረስን የመኪናችንን ጉልበትና ጥንካሬ የሚፈትን የመጀመሪያው ከባድ ጭቃ አገኘን፡፡

መኪኖቻችን ሰነጣጥቀው እየወጡ ወደ ግራ ወደ ቀኝ እየደነሱ እንደ ሰንጋ በሬ ሽንት ዝምዝምዝ ጉዞ አድርገው ሁሉም ፈተናቸውን በብቃት ተወጡ፡፡ የጭቃ ጉዞ አስፈሪና አዝናኝ ነበር፡፡
የክልሉ ገጠር መንገድ ሥራ ድርጅት ሶዶ ድስትሪክት ጥገና የጀመረ ቢሆንም ሥራው ሰርገኛ መጣ ይመስላል፡፡ አከባቢው ከፍተኛ ደጋ በመሆኑ የዝናብ ወቅት ሳይመጣ ቀድሞ መንገዱን በአግባቡ መጠገን በተገባ ነበር፡፡

ያኪማ ቅ/ጊዮርጊስ፣ ሕገ ኦሪት የተፈፀመባትንና የኢትዮጵያዊው ጀግና አባታችን አቡነ ጴጥሮስ (አላምቦ) ዲያቆን ሆነው ያገለገሉባት ያኪማ ቅ/ማርያም ቤ/ያንን ጨምሮ በርካታ ገዳማትና አድባራትን እያለፍን ወደ ከፍታ ማማው ተጓዝን፡፡

በዎላይታ ከባድ ወንጀሎችን የፈፀሙ በተለይ በሀገርና በሕዝቡ ላይ ክህደት የሚፈጽሙ አካላት ላይ የሚፈረደው የሞት ቅጣት (Capital punishment) የሚፈፀምባትን ስፍራ ያኪማ ሆሎዞ ደረስን፡፡

ተራራውን ተራምዶ ቀጥታ መውጣት ይከብዳል፡፡ ይህ እውነታ በአከባቢው በዚህ መልኩ ይገለፃል፦ ” ሀሪያው ሀሪኪሣ ካሪያ ሃላል ቦሎቶ ሄሜቲን ኬሴና ቢታ ያኪማ ሆሎዞ” ፡፡ እንዲሁም “ማቶይ ባይና ቆሪያ ማጫራይ ባይና ማሻን ጎራኢዮ ሶሁዋ” በማለት፡፡

በጉዟችን ድባብና በሀገሬው ልምላሜ እየተገረምን በርካታ ቁጥር ያላቸውን ትንንሽና በጣም ንጹህ ወንዞችን ያለ ድልድይ እየተሻገርን ተጓዝን፡፡

ቶሎ ቶሎ የሚቀያየረው የአየር ጠባይ ሲለው ግጥም አድርጎ አከባቢውን ማየት እንዳንችል አድርጎ ሲያጨልምብን ሲያሻው ከፈት ሲያደርግ በጉሙ ተግባር እየተገረምን በግራ በኩል ማዶ አሻግረን ታላቁን ወንድም የቁጫ ምድር እየቃኘን ወደ ፊት ነጎድንና ከዎላይታ ሶዶ ከተማ 54 ኪ/ሜትሮችን ተጉዘን ወደ ካዎ ኮይሻ ወረዳ ዋና ከተማ ላሾ ደረስን፡፡

ወደ ከተማው መግቢያ ስንደርስ በስተ ቀኝ በኩል የ44ኛው የዎላይታ ካዎ ሣና ከነበሯቸው ሁለት ቤተመንግሥቶች ዎሼ አልዳዳ ቀበሌ ክልል ውስጥ ዲንቻ ተራራ አናት ላይ ያለውና ትልቁ ቤተመንግሥታቸው የነበረበት “ዎሼ ጋሩዋ” ይገኛል፡፡

ሁለተኛው ቤተመንግሥታቸው ካዎ ኮይሻ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ኮይሻ ተራራ አናት ላይ የነበረ ሲሆን ወረዳው መጠሪያ ያደረገው የዚህን ቤተመንግሥት መገኛ ሥፍራ ስያሜ ነው፡፡

ትንሽ እንደ ተጓዝን የታላቁ ካዎ ሣና መካነ መቃብር የሚገኝበትን የላሾ ቅ/በዓለወልድ ቤ/ያን ደረስን ታሪካዊ ኑዛዜያቸውንና ታሪካቸውን እያሰብን ወደ ፊት ተጓዝን ፡፡ ካዎ ሣና የወርቅ ማጫሚያ ጦርና ጋሻ ይዘው ሀገር የማቅናት ተልዕኳቸውን ለልጃቸው ካዎ ኦጋቶ ለማስተላለፍ ወደ ጠላት አዙራችሁ አቁማችሁ ቅበሩኝ ባሉት መሠረት ቆመው ተቀብረዋል፡፡

ከላሾ ከተማ ወደ ዋሙራ የሚወስደውን ዋና መንገድ ትተን ወደ ግራ ታጥፈን ዝግጅታችንን ወደ ምንከውንበት ሥፍራ ለመድረስ የመጨረሻውን እስትንፋስ ሰብስበን የመኪናችንን ተጨማሪ ጉልበትና ሣንባ የሆነውን ሪዶታ (lock) H4 በሚለው ላይ አስረን ተንደርድረን ከተንጣለለዉ ከፍታ ማማ ላይ ወጣን፤ ቦሎላ ጉታራ፡፡

ከዚህ ሥፍራ ፊት ለፊት ላይ የካዎ ሣና የጓሮ አትክልት ማብቀያ ሥፍራ ይታያል፡፡”ሣንታ ኬታ” የሚል ስያሜ አለው፡፡

የአከባቢው ቅዝቃዜና ጉም እጅግ ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሳ ለመተያየት የሚተፋፈሩና ለመተያየት የማይፈቀድላቸውን ያገናኛል፡፡ ለምሳሌ፦ ከጋብቻ በኃላ መልስ ያልጠራ ወላጅና (አይፊያ ጋቲቤናጋ) አማቹን አቀርቅረው እየተጓዙ ድንገት ፊት ለፊት ይገናኛሉ ይባላል፡፡ “ቦሉዋ ቦሎቴራ ጋቲያ ቦሎላ ሜጎ” ተብሎ ይገለጻል፡፡

የሂዶታ ፈረሰኞች ማህበር በቁጥር 50 አባላት ያሉት የፈረስ ግልቢያ ውድድር እያደረጉ በከፍተኛ ደረጃ አቀባበል በማድረግ አዝናንተውናል፡፡ “ታላማ ጊዮ ቆሊቺያ ፓራ ጎዳው (ተስፋሁን አዋሾ የወረዳው ባህልና ማስታወቂያ ጽ/ቤት ኃላፊ) ስለ መልካምና ቀና ተግባሮችህ አመሰግናለሁ)፡፡

በዎላይታ ባህል ከሚከወኑ ባህላዊ የጋብቻ ዓይነቶች አንዱ በሆነው በፈረስ ታጅቦ በሚፈፀመው ሥርዓት (ፓራ ቡላቻ) መሠረት የሙሽሮቹ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በደማቅና ባማረ ሁኔታ ተፈጽሟል፡፡

የካዎ ጦናን ግርማ ሞገስ ተላብሶ ባማረው ቁመና መልከ መልካሟን ሙሽሪት በባህላዊ አለባበስ በደመቁ ሚዜዎቻቸው ታጅበው ብቅ ሲሉ ከአከባቢው ውበት ጋር ተደምሮ የፈጠረብን ስሜት የተለየ ነበር፡፡ ከልብ የማይጠፋ ደስታ፣ ትዝታና ፖስት ካርድ የሚመስሉ የፎቶግራፍ ማስታወሻዎችን አስቀርተናል፡፡

በአጭሩ የተዋበ ለበርካታ ወጣቶች የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በምን መልኩ መፈፀም እንዳለባቸው፣ የዞኑ ባህልና ማስታወቂያ መምሪያ ባህላችንን በማስተዋወቁ በኩል ከእንቅልፉ እንዲነቃና የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የብሔሩን ባህል ከመጠበቅ አንፃር ያለውን ከፍ ያለ ሚና በአግባቡ እንዲወጣ የቤት ሥራ የሰጠ የደመቀና ያማረ ሠርግ ሆነ፡፡

የፈረስ ግልቢያ ትርዕት፣ የሙዚቃ ዝግጅት በተለይ ደግሞ “ላላሺሞ- ኤኪዲ ይዳ ናኢዮ – – -” እየተባለ ሙሽራው ሙሽሪትን ይዞ ከወጣ በኃላ የሚዘፈነው ዘፈን በይበልጥ ይመስጣል፡፡

ሎጎሙዋ፣ ፒጫታ፣ ቆጪቆጩዋ፣ ሙቿ፣ ኡንጫ ኦይታ፣ ቃዬ ኣሹዋኔ ሣውዋ ጫዲዶ ዳታ ወዘተ እጅ የሚያስቆረጥሙ ጣፋጭ ምግቦች የምሳችን አካል ነበሩ፡፡”ሙቿዋኔ ሙጧ ኡስቲያጌቱ ናኣው” የሚለውን አባባል በተግባር ፈፀምን፡፡ የተመገብንበት ዬቻ (የእንሰት ቅጠል ኮባ) ለሙሽሮች ልምላሜን ስለ መመኘታችን ማሳያ ነው፡፡

የዎላይታ ባህላዊ መጠጥ ፓርሧ (ቦርዴ) ከረጅም ጊዜ በኃላ በትክክለኛው ጣዕሙ አገኘሁ፡፡ ናቺሣ ፓርሧ!!

ለዛ ያለው ሙዚቃ በጫቻ ዛይያ፣ ዲኒኪያ፣ ኡልዱዱዋ፣ ካንባና ካራቢያ ተቀነባብሮ ወገባችንን ክፉኛ ፈትኗል፡፡

ትኩረት የሚሹ ነገሮች 1) ይህ ታሪካዊ ሥፍራ ከሶዶ ቅርብ ከመሆኑም በአከባቢው የሚያዝ የሚጨበጥ ነገር ሁሉ ታሪክ ያለው ቅርስ ነው፡፡ በተፈለገ ጊዜና መጠን ለመጎብኘት አቅም በፈቀደ መጠን ታሪኩን የማስተዋወቅ፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት በተለይ መንገድ በልዩ ትኩረት ሊታይ ይገባል፡፡

2) እጅግ የሚያሳዝነውና ተስፋ ያስቆረጠን ነገር ይህ የሚያምረው የሕዝብ ሜዳ ጉታራ በሊዝ ሊሸጥ ድንጋይ ተተክሎ አየን፡፡ ይህ ታሪክ ይቅር የማይለው በሕዝባችን ታሪክ ላይ የሚፈፀም ግፍ ነውና የሚመለከታችሁ አካላት አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

የተለያዩ ቅርሶች የሚገኙባቸው አከባቢዎች ከከተማ ዕድገትና መሰል ነገሮች አንፃር የተለየ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ ፡፡

3) እንሰት ድርቅን የሚቋቋም ለሰውም ለእንስሳትም ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጥ በመሆኑ ” ኡታ ኣላ” በደንብ ስላየሁ ደስ ብሎኛል፡፡ ቀርከሃም ከእንሰት ቀጥሎ በአከባቢው በስፋት የሚገኝ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ቢደረግ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

በህግ ጠበቃና የታሪክ ፃሃፊ አምሳሉ መሰኔ(ቃቆ) የተፃፈ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: