ዛሬ በፌደራል እና በክልል ደረጃ የተደረገ ከፍተኛ የሹም ሽረት መረጃ

ዛሬ አቶ ደመቀ መኮንን ከምክትል ጠቅላይ ምኒስትርነታቸው በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ምኒስትርነት ሥልጣንን ደርበው እንዲሰሩ ተሾመዋል። አቶ ገዱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሆነው ተሾመዋል።

የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሆነው የተሾሙት ጄኔራል አደም መሐመድ ከኃላፊነት ተነስተዋል። ምክትላቸው የነበሩት ጄኔራል ብርሀኑ ጁላ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሆነዋል።

ባለፈው ሳምንት ጥሪ ተደርጎላቸው የኢትዮጵያን ጦር የተቀላቀሉት ሌቴናል ጄኔራል አበባው ታደሰ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆነዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ የብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነዋል።

በዛሬው ሹም ሽር እና ሽግሽግ አቶ ደመላሽ የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሾመዋል። በውሳኔው መሰረት የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ከኃላፊነት ተነስተዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው ስብሰባ በአቶ ተመስገን ምትክ የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩትን አቶ አገኘሁ ተሻገርን ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል።