
በጎፋ ዞን ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ሲያሰራጭ የነበረው ግለሰብ በ 11 ዓመት ፅኑ እስራትና በ 6 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት መቀጣቱን የጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ ገልጿል።
የጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት ባዋለዉ ችሎት ከ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ውስጥ የፌደራል ፣ የክልል የዞንና የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎችንና የሥራ ሂደት ማህተሞች አስመስሎ በማሰቀረጽ እና ሐሰተኛ የመንግስት ሰነዶችና የትምህርት ማስረጃዎችን ሲያሰራጭ የነበረው ግለሰብ ላይ ውሳኔ ማስተላለፉን የዞኑ ፍትህ መምሪያ ገልጿል።

ተከሳሽ ይሁን በላቸው አድራሻው ምዕራብ አሪሲ ዞን ሲሆን ተከሳሽ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 በመተላለፍ ሁለት ክሶች የቀረቡበት ሲሆን ክስ1 አንቀጽ 23/1/ሀ በመተላለፍ ለራሱ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሀሰተኛ ሰነዶችን በማሰራጨት መከሰሱ ተገልጿል።
1ኛ የሴንትራል ጤና ኮሌጅ በፋርማሲ ቴክኒሻን ዲፕሎማና የመጀመሪያ ዲግሪ የተሰጠው መሆኑን የሚገልጽ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ
2ኛ ከኢትዮጵያ ምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የተሰጠ ሐሰተኛ የሥራ ልምድ
3ኛ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጣና ኤጀንሲ የልህቀት ማዕከል የፋርማሲ ሙያ የተሰጠ ከተገለጹት ተቋማት ህጋዊ መንገድ የተሰጠ በማስመሰል ካዘጋጀ በኋላ ራሱ ቀረጾ ያዘጋጀውን ሀሰተኛ ማህተሞች በመምታት አስመስሎ ይዞ ሲንቀሳቀስ ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ ከሐሰተኛ ሰነዶችና ማህተሞች ጋር እጅ ከፍንጅ የተያዘ በመሆኑ በፈፀመው መንግሥታዊ ሰነዶችን አስመስሎ በማዘጋጀት ወንጅል የተከሰሰ ሲሆን
በክስ 2 በአንቀጽ 23/3 በመተላለፍ ቀኑና ስዓቱ በማይታወቅበት በነሐሴ ወር 2013 ዓ/ም በጎፋ ዞን ጤና መምሪያ በመቅረብ ከፌደራል ምግብና የመድሃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን በሲኒየር ዲራጊስት የሙያ ስራ ፍቃድ የተሰጠው በማስመሰል ራሱ ያዘጋጀውን ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዞ በመቅረብ የግል የጤና አገልግሎት ድርጅት ባለሙያ የግዴታ ዉል በመግባት በዶክተር ስሜነህ በላይ ክሊኒክ የመድሃኒት ባለሙያ ሆኖ እንዲሰራ ፍቃድ አግኝቶ ሲሰራ ቆይቶ ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ ከነ ሐሰተኛ ሰነዶችና ማህተሞች እጅ ከፍንጅ የተያዘ በመሆኑ በፈፀመው በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል ወንጀል ተከሶ ለጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅረቦ ክሱን ሳይቃወም ወንጀሉን አልፈጸምኩም ብሎ ክዶ ቢከራከርም ዐቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ በኤግዚቢትነት ከእጁ የተያዙ ማህተሞች አቅርቦ በመከራከር ተከሳሹ መከላከል አለመቻሉን ተገልጿል።
ዛሬ መስከረም 20 ፣ 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሁለቱም ክሶች ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በ 11 ዓመት ጽኑ እስራትና በ 6,000 ስድስት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ መቅጣቱን የዞኑ ፍትህ መምሪያ ገልጿል።
የዞኑ ፍትህ መምሪያ የህግ የበላይነት እንድከበር ከከተማ አስተዳደር እስከ ዞን ድረስ የተባበራችሁ የፍትህ ሴክተር ባልደረቦች ፣ የጸጥታ ኃይሎችና ከጤና መምሪያ ለጉዳዩ ስኬት ከፍተኛ ርብርብ ላደረጋችሁ አካላት ልባዊ ምስጋና አቅርቧል።