ወጣት ብሩክ በቀለ ይበላል። በዎላይታ ሶዶ ተወልዶ ነው ያደገው። ወጣቱ በዎላይታ ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። የአልሙኒየም ብረቶችን እና ሌሎች ቁሶችን በመጠቀም የሰራውን አውሮፕላን ለማብረር ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ይናገራል። ለዚህም የፈጠራ ስራ የሚመለከታቸው አካላት ዕውቅና ሰጥተውታል። ይህን የፈጠራ ስራውን ይዞ ነው በአውደ ርዕዩ የቀረበው።

በአዲሱና በዘመናዊ የኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም በቀለበት ቅርጽ በተገነባው ህንጻ ውስጥ አዳዲስ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል። ድሮኖች፣ የሮቦት ካፌ፣ አነስተኛ አውሮፕላንና ወታደራዊ ሮቦቶችና መሰል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች እዚህም እዚያም ይታያሉ።

ከአንዱ ወደ ሌላው የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሲጎበኙ አጃኢብ የሚያስብል ግርምትን ይፈጥራል። ለካስ እንዲህም ያለ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራ በኢትዮጵያ ይሰራል ብለው ይደነቃሉ። የሳይንስ ፈጠራዎቹ እጅን በአፍ የሚያስጭኑና የነገዋ ኢትዮጵያን ተስፋ የሚፈነጥቁ ናቸው።

የሳይንስና የቴክኖሎጂ አውደ ርዕዩ እንደ እኔ አይነት ወጣቶች ዓላማቸውን እንዲያሳኩ ያግዛል የሚለው ወጣት ብሩክ፤ አዳዲስ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች የቀረቡበት በመሆኑ ከሌሎች ትምህርት እንዲቀስም ሌሎች ደግሞ ከእኛ ልምድና እውቀት እንዲቀስሙ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ብሏል።

በተለይ አውደ ርዕዩን የሚጎበኙ ወጣቶችና ህጻናት ሳይንሳዊ የፈጠራ ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ያበረታታል፤ ያነቃቃል፣ ያነሳሳል። ይህም ነገ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትደርስ ያስችላል ሲል ገልጾልናል።

ወጣት አዋድ ሳልህ በማይክሮኒክ ኮሌጅ የኮምፒተር ሳይንስ ትምህርት የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ነው። በአውደ ርዕዩ ለማየት ጓጉቶ ወደ አዲሱ የኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም እንደመጣ ይናገራል። በአውደ ርዕዩ ተስፋ የሚሰጡ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አይቻለሁ። እነዚህ ስራዎች በቀጣይ ብዙ ከተሰራባቸው በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ለውጥ የሚያመጡ ናቸው። ይህም ብቻ ሳይሆን በተለይ አዲሱን ትውልድ የሚያነቃቃ ነው ብሏል።

እኔ በግሌ ተስፋን አጭሮብኛል። ብዙ ያሰብኳቸውን ስራ እንዳሳካ ሞራል ሰጥቶኛል። በተማርኩበት ሙያ የተሻለ ሀገርና ህዝብ የሚጠቅም ስራ ለመስራት ዝግጁ እንድሆን አድርጎኛል ብሏል ወጣቱ።

ዛሬ በዓለም ላይ የሰለጠኑ ሀገራት የቴክኖሎጂና የሳይንስ ውጤቶቻቸው ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ናቸው የሚለው በኢትዮ-ቴሌኮም ኔትዎርክ ኢፍራስትራክቸር ስትራቴጂ ዳይሬክተር ዮሀንስ ጌታሁን፤ ምርታማነታቸውንና የአሰራር ውጤታማነታቸውን እያረጋገጡ የሚገኙት በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ መሆኑን ይናገራል።

ኢትዮጵያም ይህን ቴክኖሎጂ በስራ ላይ በማዋል ብዙ ጅምር ስራዎችን እየሰራች መሆኑን ገልጾ፤ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች አውደ ርዕዩ ይህንኑ የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጾልናል። ኢትዮ-ቴሌኮም ኢትዮጵያን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ማሸጋገር የሚያስችሉ ፈርጀ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኘና ይህንኑ የቴክኖሎጂ አዳዲስ አገልግሎቶቹን በአውደ ርዕዩ ይዞ መቅረቡንና እያስተዋወቀ መሆኑን አመልክቷል።

ብዙ ዓለም አቀፍ የሳይንስና የቴክኖሎጂ አውደ ርዕዮች ተጋብዤ በአካል ተገኝቼ ተመልክቻለሁ የሚለው ዳይሬክተሩ፤ በኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው አውድ ርዕይ እየታዩ ያሉ አዳዲስ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ትዕይንቶች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ተስፋ የሚሰጡ ናቸው ሲል ነግሮናል።

የማዕድን፣ የግብርናን፣ የጤናን፣ የትምህርትንና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ሊያዘምኑና ሊያቀላጥፉ የሚችሉ 120 የሚደርሱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የቀረቡበት አውደ ርዕይ ነው ብሏል።

አውደ ርዕዩ ለተመራማሪዎችና ለታዳጊዎች ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ገልጾ፤ ከአፍሪካም ሆነ ከአሜሪካ የመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች አውደ ርዕዩን አይተው የሰጡት አስተያየት እንደ ሀገር የሚያነቃቃና የሚያበረታታ ነው። በቴክኖሎጂና በፈጠራ ስራም ተስፋ እንዳለን ነግረውናል። ይህን አውደ ርዕይ በተለይ ለቴክኖሎጂ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች መጥተው ቢያዩት ትልቅ ተስፋና ብርታት የሚያገኙበት ነው ሲል መልዕክት አስተላልፏል።

አውደ ርዕዩ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ ሲሆን፤ ኢትዮ ቴሌኮም፤የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በጋራ ያዘጋጁት መሆኑ ታውቋል ስል ኢድፕ ዘገባ ያመለክታል።

1 thought on “የሳይንስና ቴክኖሎጂው ማርሽ ቀያሪ ፈጠራዎች ወጣት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *