የጣና ፎረም ጉባኤ በአፍሪካ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ዕድሎችን የፈጠረ ነው ሲሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡

አቶ ኃይለማሪያም በመጪው ጥቅምት ወር አጋማሽ በባሕርዳር ከተማ በአፍሪካ የጸጥታ ጉዳች ዙሪያ የሚመክረው የጣና ፎረም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ÷ የጣና ፎረም ጉባኤ ከተመሰረተ 10ኛ ዓመት ማስቆጠሩን ጠቁመው÷ በቀጣዩ ጉባኤ የአፍሪካ ጸጥታ ጉዳዮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሀሳቦች የሚነሱበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መድረኩ በአፍሪካ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን ለመቅርፍ የሚቀራረብ ሃሳብ ያላቸው ባለድርሻ አካላት ግልጽ እና ተዓማኒ በሆነ መንገድ የሚመክሩበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋልም ነው ያሉት፡፡

አያይዘውም ጉባኤው በአፍሪካ አህጉር የኮሮና ወረርሽኝ እና የዓየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተግዳሮት እየሆኑ በመጡበት ጊዜ የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ወቅቱ የሩሲያ- ዩክሬን ግጭት በነዳጅ እና ማዳበሪ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በማስከተል ውስብስብ ችግር የፈጠረበት ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ እና ሳህል ቀጠና አካባቢዎችም የአዳዲስ አሸባሪ ቡድኖች ማዕከል እየሆኑ መምጣታቸውን ነው የገለጹት፡፡

ፎረሙ በአፍሪካ አህጉር ለሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች የመፍትሄ ሃሳቦችን በማቅረብ ዘላቂ እና የተረጋጋ ሰላም ለማስፈን ያለመ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ፍስሃ ሻውል በበኩላቸው÷ለቀጣዩ ጣና ፎረም ጉባኤ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መከናወኑን እና ለሚሳተፉ አካላት ጥሪ መደረጉን አመላክተዋል፡፡

በፎረሙ የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ ከ300 በላይ እንግዶች እንደሚሳተፉ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ሲል (ኤፍ ቢ ሲ) ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: